Monday, December 1, 2014

ተመስገን ደሳለኝን ተቀበልኩት (ሕገ-መንግስት ሆይ የት ነው ያለኸው?)

ከክንፈሚካኤል ደበበ በረደድ (አበበ ቀስቶ)
ከዝዋይ ወህኒ ቤት

ቀኑ ቅዳሜ በመሆኑ ቤተሰቦቻችን እኛን ለመጠየቅ /ፈርዶባቸው የለ/ ወደ ዝዋይ ወህኒ
ቤት የሚመጡበት ሰዓት ደርሶ፣ ተጠርተን እንደወጣን፣ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ የጠየቅናቸው
ነገር ቢኖር፣ ምን አዲስ ነገር አለ የሚለውን የተለምዶ ጥያቄያችንን ነበር፡፡
በዕለቱም የመጣልን የምስራች ልበለው ዜና አሊያም መርዶ ጋዜጠኛ ተመስገን ሦስት
(3) ዓመት ተፈረደበት የሚል ነበር፡፡ በዜናው አልተደነቅንም፤ አልተገረምንም፤ ምክንያቱም
በሥልጣን ላይ ያለው የህወሓት /ኢህአዴግ/ አምባገነን መንግስት፣ ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከዚህ ሌላ ሊሸልመው
የሚችለው መልካም ሽልማት /ሜዳሊያ/ የለውምና፡፡ በነገራችን ላይ ዜናው ለኔ ፍጹም አልገረመኝም፤ እገረም የነበረው
አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት ተመስገንን በነጻ ቢለቀው ነበር፡፡
የሆነው ሆኖ፣ ከቤተሰብ ጥየቃ ተመልሰን ገና ምሳ በልተን አረፍ እንዳልን ግን፣ የሰማነውን ዜና እውነታ በአካል
የሚያረጋግጥልን አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ፍራሹን ተሸክሞ እኛ አለንበት ጭለማ ቤት /የቅጣት ቤት/ ድረስ
መጣ፡፡ ዓይኔን ማመን እስቲያቅተኝ ድረስ ተጠራጠርኩ፤ ግን ሆነ፡፡ ተመስገን መጣ፡፡ እናም ውለን ሳናድር ተመስገን
ደሳለኝን ተቀበልኩት! እነሆ ተመስገን ዝዋይ ከመጣ ዛሬ 15 ቀን ሆነው! ... ሕገ-መንግስት ሆይ የት ነው ያለሽው!?
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዳሉ፤ እግረ መንገዴን እስቲ አንድ ገጠመኜን ደሞ ላጫውታችሁ፡፡ ህወሓት
/ኢህአዴግ/ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ በሁኔታው ያልተደሰትን ጓደኛማቾች ተሰባሰበን፣ ከኛ ቀድመው ከብላቴ
ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ወደ ኬንያ የተሰደዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችንና ሌሎች ወገኖቻችን ተቀላቅለን ለመታገል
በመወሰናችን ተሰባስበን፡፡ ወደ ኬንያ የስደት ጉዞ ጀመርን፡፡ ይህ የሆነው ግንቦት 23 ቀን 1983 ዓ.ም ከሃያ ሦስት ዓመት
በፊት ነው፡፡

ታዲያ በዚህ ጉዟችን በአጋጣሚ አገረማርያም ከተማ የማረፍ ዕድል ገጥሞን ነበር፡፡ እዚያም አቶ አብርሃም ያየህና
ጓድ ጌታቸው ሮበሌ (የአኢወማ ሊቀመንበር የነበሩ) ወደ ኬንያ ለመሸሽ በዚህ ሲያልፉ ተይዘው ያቤሎ ከተማ ፖሊስ
ጣቢያ ታስረዋልና እባካችሁ ያቤሎ ከተማ ጐራ ብላችሁ አስፈትታችሁ ይዛችኋቸው ሂዱ የሚል የወገን ጥቆማ ደረሰን፡፡
እኛም ይህን ጥቆማ ተቀብለን በሰማነው ዜናም ተደናግጠን ጉዟችንን ወደ ሞያሌ በማድረግ፣ ከምሽቱ 3፡30
ሰዓት ላይ ያቤሎ ከተማ ደርስን፡፡ በወቅቱ ህዝቡ በነበረው /በተከሰተው/ ሁኔታ እጅግ ተቆጥቶ ከተማዋን ከዘራፊና
ከዝርፊያ ለመጠበቅ በሚል ተደራጅቶ በየተራ ከተማውን ይጠብቅ ስለነበር መኪናችንን አስቁመው ከመሸ ከተማ መግባት
እንደማንችል በትህትና አስረድተውን፣ ከከተማው ወጣ ብለን በማደር፣ ማለዳ መግባት እንደምንችል ነግረውን፣
ተስማምተን ከከተማው ወጣ ብለን አደርንና ጠዋት ማለዳ ላይ ወደ ያቤሎ ከተማ ገባን፡፡
ወዲያውም ወደ ያቤሎ ፖሊስ ጣቢያ ሄድን፤ የታሰሩትን አቶ አብርሃም ያየህና ጓድ ጌታቸው ሮበሌን እንዲፈቱና
እኛ ጋር ወደ ኬንያ እንዲሄዱ እንፈልጋለን ስንል በወቅቱ ለነበሩ የፖሊስ አባላት ጥያቄ አቀረብን፡፡ ፖሊሶቹም ፍጹም
ትህትና በተሞላበት ሁኔታ ተቀብለውን ካነጋገሩን በኋላ፣ ሁለቱ ሰዎችና ሌሎች አባሪዎቻቸው ትናንትና ተፈተው ወደ
ሞያሌ ሔደዋል አሉን፡፡ እኛም ለፈጸሙት መልካም ተግባር አመሰግነን፣ ጉዟችንን ወደ ሞያሌ ቀጠልን፡፡
ልብ አድርጉ! ... ያኔ በዚያ በ20ዎቹ የመጀመሪያ እድሜ ላይ የነበርን ወጣቶች የታሰሩ ወገኖቻችን ካልተፈቱ
በሚል ነበረ ስንቆጣ የነበረውም፣ የጮህነውም፤ ዛሬ በጉልምስና እድሜያችን ግን በግፍ በወህኒ ቤት ተወርውረን ምንም
ማድረግ ባንችል፣ ልክ እንደኛ የግፍ ሰለባ የሆነውን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ተቀበልነው፡፡ ከነዚያ አገራቸውን
 ተመስገን ደሳለኝከውድቀት ለማዳን ሲሉ ብላቴ ከዘመቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል ሁለቱ አሁን ከኔ ጋር ባንድ ቤት ሆነው በእስር
እየማቀቁ ነው፡፡
ልብ በሉ! ... ተመስገን ደሳለኝን የተቀበልነው ቤተመንግስት አይደለም፤ ሸራተን ወይም ሒልተን ባለአምስት
ኮከብ ሆቴል አይደለም፡፡ ካምቦሎጆ አይደለም፡፡ ከ23 ዓመታት በኋላ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳናሳይ፣ ያችን እንኳ በዚያች
ዕድሜያችን ያሳየናትን የፍቱልን ጥያቄ ማቅረብና እምቧ-ከረዩ ማለት አቅቶን፤ የነጻነት፣ የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የእኩልነት
ጥያቄያችን ባለመመለሱም የተነሳ፣ እድለ ቢስ ሆነን ነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን የተቀበልነው፤ በዝዋይ ወህኒ ቤት
በሚገኝ 9ኛ ቤት በሚባል ጭለማ ቤት /የቅጣት ቤት/ ውስጥ ሆነን ነው፡፡ እረ ጐበዝ አንድ በሉ!... ይህ ነገር ማቆሚያው
የትና መቼ ነው?...
ተመስገን ደሳለኝ በአካል ወደኛ የመጣው ቅዳሜ በ22/02/2007 ዓ.ም ይሁን እንጂ፣ በተደጋጋሚ “ያልተገሩ
ብዕሮችና!” ሌሎች የኢቲቪ ዶክመንመተሪ ፊልሞች፣ እንዲሁም በኢቲቪ የሚዲያ ዳሰሳ ፕሮግራሞች አማካኝነት
ሳይወሰንበት በፊት በሀሳብ ከኛ ጋር ተቀላቅሎ ነበር፡፡
እኛም ከነዚህ ዘገባዎች በመነሳት፣ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ዕጣ-ፈንታ የተለመደው የግፍ እስራት ሊሆን
እንደሚችል ከህወሓት /ኢህአዴግ/ ባህሪ የተነሳ፣ መገመት ብቻ ሳይሆን፣ ሙሉ ለሙሉ አምነን ነበር፡፡ የሆነውም ደግሞ
ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም በአፍሪካ ውስጥ፣ በተለይም በእኛይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣
እንዲሁም ለሰው ልጆች የመናገርና የመጻፍ ነጻነት የሚታገል ታጋይ ሁሉ፣ ዕጣ- ፈንታው እስራት፣ ግርፋት፣ ስደት እና ሞት
ብቻ ነው፡፡ ተሜም የመረጠው ለነጻነት፣ ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለዲሞክራሲ እየታገለ የሚመጣውን መከራ መቀበልና
የሚከፈለውንም ዋጋ መክፈል ብቻ ነው፡፡ “የፈራ ይመለስ!” አይደል ያለው፡፡ ቃሉንም በተግባር አደረገው፡፡ ብራቮ ተሜ!!!
ተመስገን ፍራሹን ተሸክሞ እኛ ወዳለንበት ጭለማ ቤት /ቅጣት ቤት/ ሲመጣ፣ መጀመሪያ የያሁት እኔ ነበርኩ!...
በቀጥታ ተንደርድሬ ተመስገንን ተቀበልኩት፡፡ ሌላ ምንም ምርጫ የለኝም፡፡ እሱም ቢሆን እኔንና ጓደኞቼን ሲያይ፣ ለቤቷ
እንግድነት አልተሰማውም፡፡ ከዚያማ ምን ልበላችሁ፣ የተራብነውን መረጃ አንድ ባንድ አብራራልን፤ ዘረገፈልን ማለት
ይቀላል፡፡
ለኔ እንደ ምግብ ዝርዝር (ሜኑ) የተሰናዳ - ዝርዝር መረጃ ሳገኝ፣ በ3 ዓመቱ የእስራት ዘመኔ የመጀመሪያዬ
በመሆኑ ተደስቻለሁ፡፡ እንደውም የተሰማኝ እርካታ ቃላት ሊገልጸው ከሚችለው በላይ ነው፡፡ በ21ኛው ክ/ዘመን መረጃ
የተራብነውና የተቸገርነው የኢህአዴግ መንግስት ባለንበት እስር ቤት ከኢቲቪ ውጭ ማየትና ማድመጥ ስለከለከልንና
ስላፈነን ነው፡፡
ሰው መቼም ወደ እስር ቤት ይምጣ ባይባልም እንኳ፣ በተለይም ለወዳጅ ይህን ባይመኙለትም፣ እንደ ተመስገን
ያለ አንጀት አርስ የመረጃ ሰው ለአንድ- አንድ ቀን ቢመጣልን የእስራት ጊዜያችንን ያጣፍጥልን ነበር፡፡ ግን! ... ለምን? ...
ለምን?... ለምን ይምጣ!?
ለትኩስ መረጃ ካለኝ ጉጉት አንጻር ይህንን ብልም እንኳ፣ የተመስገን ደሳለኝ መታሰር ለእኔ ፍጹም- ፍጹም
ተገቢም አስፈላጊም አይደለም፡፡ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በውሳኔያቸው በፍጹም ተሳስተዋል፡፡ ኢህአዴጎች ሆይ!...
ተመስገንን እንዲታሰር በመወሰናችሁ በዲሞክራሲ ላይ እጅግ ተሳልቃችኋል!... ድሮም የሌላችሁን የመንግስትነት ግርማ
ሞገስ በድጋሚ አጥታችሁታል፡፡ የራሳችሁ ሕገ-መንግስት በአንቀጽ 29 ላይ የሚደነግገውን ድንጋጌ በመጣስ ለሕገ-
መንግስታችሁ ክብር አሳጥታችሁታል … ኢህአዴግ ሆይ ሕገ-መንግስትህ ወዴት ነው ያለው፤ ፈልገህ ካገኘኸው ላክልኝ! ...
እናም ወገኖቼ! በተመስገን ደሳለኝ ላይ የተጣለውን የግፍ ውሳኔ አጥብቄ እቃወማለሁ! … ደግሜ- ደጋግሜ አወግዛለሁ!››
ከ5 ዓመት በፊት በወጣ አንድ “አዲስ ራዕይ!” በሚባል የኢህአዴግ መጽሔት ስለመተካካት በሚያወራው ጽሑፉ
ላይ “በአሁኑ ሰዓት ያለው መተካካት፣ የሰው መተካካት እንጂ፣ የፓርቲ መተካካት አይደለም፤ በአሁኑ ሰዓት የፓርቲ
መተካካት አይኖርም፡፡ እንደ ኢህአዴግ አስተሳሰብ የፓርቲ መተካካት ሊኖር የሚችለው ከ3 እና ከ4 ምርጫዎች በኋላ
ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ ኢህአዴግ በሥልጣን ላይ ያለማቋረጥ መቀጠል አለበት›› ይላል፡፡ ካልተሳሳትኩ ይህንን ያነበብኩት
ከ2002 ምርጫ በፊት ይመስለኛል፡፡ ታዲያ ይህንን የኢህአዴግ አቋምና ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ሲባል፣ ለሂደቱ እንቅፋት ይሆናሉ ተብለው
የተጠረጠሩና የተገመቱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማርያን (ብሎገሮች) ሁሉ በሰበብ-በአስባቡ
ተሰብስበው ወደ ወህኒ ቤት ይወረወራሉ፡፡ አገር ጥለው እንዲሰደዱ ይገፋሉ፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ላቀደውና ላስበው
ረዥም የሥልጣን ዘመን እድሜ እንቅፋት ናቸውና፡፡ እናም ተመስገን ደሳለኝ የዚህ የኢህአዴግ እቅድ ቀንደኛ ተቃዋሚ
ተደርጎ ስለሚወስድና ቢገፉት… ቢገፉት ከሀገር አልሰደድ ስላለ፣ በግፍ ወህኒ ቤት እንዲገባና እንዲማቅቅ ተፈረደበት፡፡
አለቀ በቃ! እውነታውና ሃቁ ይህ ነው፡፡
ከላይ በገለጽኩት ጉደኛ የኢህአዴግ መጽሔት ላይ “አንድ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ የጡረታ
መውጫ እድሜ 65 ዓመት ነው” ይላል፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች 65 ዓመት እስቲሞላቸው ድረስ መጓዝ የፈለጉትና ለመጓዝ
የወሰኑት የዲሞክራሲን መርሆዎች በመጣስና በመጨፍለቅ ነው፡፡ ዕድሜያቸው 65 እስቲሞላ ድረስም፣ እንደ ጋዜጠኛ
ተመስገን ደሳለኝ አይነት ቆራጥና የማይንበረከክ ጋዜጠኛ እጣ ፈንታው የግፍ እስራት ነው፡፡ ምክንያቱም
አልተንበረከክምና፡፡ የቆመበትን የጋዜጠኝነት መርህ ለኢህአዴግ በሚመች መልኩ አልሸጥምና፡፡ እንደውም ከዚህ
ከኢህአዴግ ፍላጎት በተቃራኒው “ጉዞዬን እስከቀራኒዮ ያደረገው!” በሚል ተፋልሟቸዋልና “እምቢ አልንበረከክም!” ብላ
ዘማሪ አዜብ ኃይሉ እንደዘመረችውም ተመስገንም እምቢ አልንበረከክም እያለ የመከራን ጽዋ በመጎንጨት፣ መጓዝን
መርጧል፡፡ ብራቮ ተሜ…በርታ!...በርታ!
እኔ ግን በዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን እጅግ አድርጌ ለአገሬና ላልታደለው ህዝቧ አዘንኩ! ... አፈርኩ! ... ምክንያቱም
በዚህ ሥልጣኔ ባበበበት ዓለም፣ የቀደሙትን ትተን በዚህ በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ20 በላይ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች
አገር ለቀው ተሰደዋል፡፡ ሦስት ጋዜጠኞች እና ስድስት ጦማርያን (ብሎገሮች) ተከሰው ፍ/ቤት እየተመላለሱ ነው፡፡
ቀደም ሲል፣ የግፍ ፍርድ የተጣለባቸው እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ እና ርዕዮት ዓለሙን
የመሳሰሉት ጋዜጠኞችን በወህኒ ቤት መማቀቅ ከጀመሩ 3 ዓመት አልፏቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ አነሰ ብሎ አምባገነኑ የኢህአዴግ
መንግስት የተዘጋና የተቋረጠ ክስ ከመንደርደሪያ ላይ አንስቶ ቆሻሻውን በማራገፍና እንደ አዲስ በመቀስቀስ ተመስገን
ደሳለኝን 3 ዓመት ፈረደበት፡፡ … እኔ ግን! ... እኔ ግን ይህንን የግፍ ውሳኔ አጥብቄ እቃወማለሁ! አወግዛለሁም!
ከተሰደዱት ጋዜጠኞች መካከል፣ ቀድሞ የኢትኦጵ ጋዜጣ ባልደረባ ሆኖ የማውቀው ሚሊዮን ሹርቤ፣ በነጻነት
እየተናገረና እየጻፈ ባገሩ መኖር አቅቶት፣ በስደት አገር መሞቱም እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ይህም ልብ ይነካል፡፡ እናንተ የነጻው
ፕሬስ አባላት ሆይ፣ የመከራ ዘመናችሁ መቼ ያበቃል! ... ስለእናንተ ልቤ በእጅጉ ያዝናል፤ … በሀዘንም ብዛት ይደማል፡፡
ነገር ግን ሁሌም በእናንተ እኮራለሁ፡፡ … በመልካም ተግባራችሁ ለአገራችሁና ለህዝባችሁ ስትሉ ስለምትከፍሉትና
ስለከፈላችሁት መራር መስዋዕትነት ልባዊ አድናቆትና ክብር አለኝ!
ኢህአዴግ ተመስገንን ለምን ፈራው?... በተመስገን የሚመራው አሳታሚ ድርጅት በተለያዩ የህትመት ውጤቶቹ
ከፍተኛ የህትመት ኮፒዎችን በማሳተም፣ በአገራችን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲያብብ ከፍተኛ አስተዋጽ
በማድረጉ የተለያዩ የፖለቲካና የእምነት ልዩነት ያላቸውን ጹሑፎች በነጻነት በማስተናገድ ከኢህአዴግ ፍላጎት ውጭ
በመንቀሳቀሱ፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ከሚታተሙ የፕሬስ ውጤቶች የተሻለ ተነባቢና በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ አመኔታ
በማትረፉ ጭምር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ይህ ኢህአዴግን ያላመመው ምን ይመመው?... በዚህ ያልተቆጣ በምን ይቆጣ?... በነገራችን ላይ የኢህአዴግን
ከፍተኛ አመራሮች ከመጽሐፉ ቅዱስ ቃል በእጅጉ የሚገባቸው “እኔ ቀናተኛ አምላክ ነኝ” የሚለው ቃል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ
ቀኑ- ቀኑና ቀናተኛ መንግስት ሆኑ፤ ቀናተኛ መንግስት ደግሞ በግፍ ከማሰር፣ ከመግረፍ፣ ከመግደልና ዜጎች አገራቸውን
ጥለው እንዲሰደዱ ከማድረግ ውጭ ስራ የላቸውምና ኢህአዴጎችም ተመስገንን በማሰር ይህንን የአምባገነንነት
መገለጫቸው በተግባር አሳዩን፡፡
እኔ ባለኝ መረጃ፣ ኢህአዴግ ፍትህ ጋዜጣን በህትመት ሂደት ላይ ሳለች ሲያግታት፣ ተመስገንና ጓደኞቹ፣ አዲስ
ታይምስ መጽሔትን ይዘው ብቅ አሉ፤ አዲስ ታይምስ መጽሔት ከሕትመት ፈቃድ ውጪ ስትደረግ ደግሞ ልዕልና ጋዜጣን
ይዘው ብቅ አሉ፤ ኢህአዴግ ይህንንም በተለመደው ስራና ጥበቡ አቋረጣቸው፡፡ ይሄኔም አይታክቴዎቹ- ተመስገንና ጓደኞቹ
ፋክት መጽሄትን እያሳተሙ በሰፊው ህዝብ ዘንድ ተነባቢነታቸው ቀጠለ፡፡ይህን ከድፍረት የቆጠረው የኢህአዴግ መንግስት በተመስገን ደሳለኝ ላይ እየከፈተ ካቋረጣቸው 126 ክሶች
ውስጥ፣ የሶስቱን ክሶች ቆሻሻውን አራግፎ ክስ ሊመሰርት አነሳሳው፡፡ ከዚያም አደርገው፡፡ በለመደው የግፍ ፍርዱም
ተመስገንን 3 ዓመት ፈርደበት፡፡ በእኔ ዕምነት ተመስገን የተቀጣውና የግፍ እስራት ተፈርዶበት ወህኒ ቤት የተወረወረው
ሮጦ ባለመድከሙ፣ ብዕሩ አልነጥፍ በማለቱ፣ በአልሸነፍ ባይነቱ እና በእልኽኝነቱ የተነሳ ነው፡፡ ሌላ ምንም ጥፋት
የለበትም፤ ሊኖርበትም አይችልም፡፡ እኔ በዚህ መልኩ ገብቶኛል! ... ወገኖቼ!... እናንተስ?
እናም ቀናተኛው የኢህአዴግ መንግስት በተመስገን ተስፋ አለመቁረጥና ቢገፋ … ቢገፋ ከአገር አልወጣ በማለቱ
በእጁ ካቴና (ሰንሰለት) ከቶ አስረው በቃ! ... ተመስገን የታሰረበት እውነታ ይሄ ነው! ... የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር
የሆንክ/ሽ/ ሁሉ፣ ሕገ-መንግስት የት ነው ያለው? ... ካገኛችሁት እባካችሁ ዝዋይ ወህኒ ቤት በሚገኘው 9ኛ ቤት /ጭለማ
ቤት/ ቅጣት ቤት ድረስ ላኩልኝ፡፡
በመጨረሻ ተመስገን እኛ በተከሰስንበት ክስ ላይ ያለኝን ተቃውሞ አስመልክቶ “ማቆሚያና ገደብ ያጣው
የምስኪኗ የእናቴ እንባ!” በሚል ርዕስ የፃፍኳትን የመቃወሚያ ሀሳብ ሚያዝያ 5 ቀን 2004 ዓ.ም በፍትሕ ጋዜጣ አትሞ
አውጥቷል፡፡ በዚህም ለተገፉና ለተበደሉ ድምጽ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር እመሰክርለታለሁ፡፡
ይህችን ጽሑፍ በማተሙ የተነሳ በፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ሚያዚያ 19
ቀን 2004 ዓ.ም አብረን ቀርበን፣ ችሎቱ ሚያዚያ 22 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተመስገንን 4 ወር እስራት ወይም
ሁለት ሺህ (2000) ብር በግፍ ሲቀጣው፣ እኔም ወግ ደርሶኝ እንደ አቅሚቲ 8 ወር እስራት ተፈርዶብኝ እንደነበር
አስታውሳለሁ፡፡ በአሁኑ የግፍ ቅጣት ጥፋተኛ ነው ብዬ እንደማላምን ሁሉ፣ ያኔም በተፈረደበት የግፍ ቅጣት አላምንም፡፡
አላመንኩበትም፡፡ ይህ የሚያሳየው ነገር ቢኖር፣ የሥርዓቱ መሪዎች አፋኝነትና ግፈኝነት አለመቆሙን ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ
የግፍ ተግባር መፈጸሙን በሥልጣን ላይ እስካለ እንደማያቆም ጭምር ነው፡፡
ለማንኛውም የተመስገንን ጥንካሬ ልታውቁ የምትችሉት እንደ እኔና እንደ ጓደኞቹ ለአስርም፣ ለአስራ አንድ ቀንም
አብራችሁ ስትኖሩ ነውና፣ እኔም አሁን በእስር ቤት ውስጥ ባለው ጥንካሬ ተደንቄያለሁ፤ ተገርሜያለሁ፡፡ በርታ! ተሜ …
በርታ! ተሜም የነጻነት ቀናችን መምጣቱን በተግባር እስኪረጋገጥ ድረስ ትግሉን እንደማያቆም ዕምነቴ ጽኑ ነው፡፡ ትግሉ
ይቀጥላል!!!

No comments:

Post a Comment