ታኀሳስ ፲፭(አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የአየር ሃይል ደህንነቶች ወደ ጠፉት አብራሪዎች ቤት በድንገት በመሄድ ፍተሻዎችን ያካሄዱ ሲሆን፣ በቤቶች ውስጥ የተገኙ ሰነዶችን፣ የበረራ ማኑዋሎችን፣ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን፣ ትጥቆችንና ሌሎችም ቁሳቁሶች ወስደዋል።
ከደህንነቶች ጋር ምንም አይነት ፖሊስ ያልነበረ ሲሆን፣ ደህንነቶች ፍተሻውን ለማካሄድም የፍርድ ቤት ማዘዣ አላሳዩም። የመከላከያ ሰራዊት ባወጣው መግለጫ ሁለቱ አብራሪዎች በዋናው አብራሪ ተገደው መጥፋታቸውን ቢገልጽም፣ ከዋና አብራሪው ውጭ ያሉት ረደት አብራሪውና ቴክኒሻኑ ቤታቸው እንዲፈተሽ መደረጉ፣ ሚኒስቴሩ የሰጠው መግለጫ የተሳሳተ መሆኑን እንደሚያመለክት ምንጮች ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህና በመጪው ሳምንታት በድሬዳዋ ምድብ ሊደረጉ የታሰቡ የበረራ ልምምዶች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጡ ተደርጓል። ግምገማው እስኪጠናቀቅና መመሪያ እስከሚወርድ ማንኛውም የበረራ ልምምድ እንዳይደረግ የተላለፈውን ትእዛዝ ተከትሎ፣ የአየር ሃይል የደህንነት ሰዎች የተለያዩ ሰልጣኝ አብራሪዎችንና ነባሮችን እያስጠሩ በመጠየቅ መረጃ እየሰበሰቡ ነው።
የኢሳት ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት ከፍተኛ የበረራ ልምድ ያላቸው ሻምበል ሳሙኤል የህወሃት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ አየር ሃይል ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት ከሚቃወሙት የትግራይ ተወላጆች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ መቶ አለቃ ቢልልኝ ደግሞ በአየር ሃይል ውስጥ የተስፋፋውን ዘረኝነት ከሚኮንኑ አብራሪዎች መካከል መሆናቸው ታውቋል።
ሻምበል ሳሙኤል ለ12 አመታት መቶ አለቃ ቢልልኝ ደግሞ ለ7 አመታት አየር ሃይልን አገልግለዋል። በሌላ በኩል መንግስት አብራሪዎቹ ሄሊኮፕተሩን ኤርትራ አሳርፈውታል የሚል መግለጫ ቢሰጥም፣ የኤርትራ መንግስት እስካሁን ምንም አይነት መግለጫ አልሰጠም። ኢሳት ሄሊኮፕተሩ የት እንዳረፈ ለማወቅ ያደረገው ሙከራም እስካሁን አልተሳካለትም።
ባለፉት 6 ወራት ብቻ አየር ሃይል 11 ልምድ ያካበቱ አብራሪዎችን አጥቷል። ሁሉም
አብራሪዎች ከአየር ሃይል በሚጠፉበት ወቅት የሚሰጡት ምክንያት ዘረኝነት፣ የፍትህ እጦትና የአስተዳደር መበላሸት የሚል ነው።
ምንጭ ኢሳት ዜና
No comments:
Post a Comment