ከክንፈሚካኤል ደበበ በረደድ (አበበ ቀስቶ)
ከዝዋይ ወህኒ ቤት
ቀኑ ቅዳሜ በመሆኑ ቤተሰቦቻችን እኛን ለመጠየቅ /ፈርዶባቸው የለ/ ወደ ዝዋይ ወህኒ
ቤት የሚመጡበት ሰዓት ደርሶ፣ ተጠርተን እንደወጣን፣ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ የጠየቅናቸው
ነገር ቢኖር፣ ምን አዲስ ነገር አለ የሚለውን የተለምዶ ጥያቄያችንን ነበር፡፡
በዕለቱም የመጣልን የምስራች ልበለው ዜና አሊያም መርዶ ጋዜጠኛ ተመስገን ሦስት
(3) ዓመት ተፈረደበት የሚል ነበር፡፡ በዜናው አልተደነቅንም፤ አልተገረምንም፤ ምክንያቱም
በሥልጣን ላይ ያለው የህወሓት /ኢህአዴግ/ አምባገነን መንግስት፣ ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከዚህ ሌላ ሊሸልመው
የሚችለው መልካም ሽልማት /ሜዳሊያ/ የለውምና፡፡ በነገራችን ላይ ዜናው ለኔ ፍጹም አልገረመኝም፤ እገረም የነበረው
አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት ተመስገንን በነጻ ቢለቀው ነበር፡፡
የሆነው ሆኖ፣ ከቤተሰብ ጥየቃ ተመልሰን ገና ምሳ በልተን አረፍ እንዳልን ግን፣ የሰማነውን ዜና እውነታ በአካል
የሚያረጋግጥልን አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ፍራሹን ተሸክሞ እኛ አለንበት ጭለማ ቤት /የቅጣት ቤት/ ድረስ
መጣ፡፡ ዓይኔን ማመን እስቲያቅተኝ ድረስ ተጠራጠርኩ፤ ግን ሆነ፡፡ ተመስገን መጣ፡፡ እናም ውለን ሳናድር ተመስገን
ደሳለኝን ተቀበልኩት! እነሆ ተመስገን ዝዋይ ከመጣ ዛሬ 15 ቀን ሆነው! ... ሕገ-መንግስት ሆይ የት ነው ያለሽው!?
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዳሉ፤ እግረ መንገዴን እስቲ አንድ ገጠመኜን ደሞ ላጫውታችሁ፡፡ ህወሓት
/ኢህአዴግ/ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ በሁኔታው ያልተደሰትን ጓደኛማቾች ተሰባሰበን፣ ከኛ ቀድመው ከብላቴ
ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ወደ ኬንያ የተሰደዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችንና ሌሎች ወገኖቻችን ተቀላቅለን ለመታገል
በመወሰናችን ተሰባስበን፡፡ ወደ ኬንያ የስደት ጉዞ ጀመርን፡፡ ይህ የሆነው ግንቦት 23 ቀን 1983 ዓ.ም ከሃያ ሦስት ዓመት
በፊት ነው፡፡