Thursday, November 6, 2014

መልዕክት ከቃሊቲና ከቂሊንጦ


ነገረ ኢትዮጵያ

የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችና የነገረ ኢትዮጵያ የዝግጅት ክፍል አባላት ወደ ቂሊንጦና ቃሊቲ እስር ቤቶች በማቅናት እስረኞችን ጠይቀዋል፡፡ እስረኞቹ ያስተላለፉትን መልዕክት ነገረ ኢትዮጵያ እንደሚከተለው ጠቅለል አድርጋ አቅርባዋለች፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አይቀርም›› እስክንድር ነጋ

በማህበራዊ ድረ-ገጽም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች መልካም ልደት ለተመኛችሁልኝ ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የቡርኪናፋሶው አምባገነን መውደቁን በመስማቴ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ይህ ለእኔ ውድ የልደት ቀን ስጦታየ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ለውጥ የሚቀር አይደለም፡፡ የእኛ ችግር ከማንም የባሰ ነው፡፡ ቱኒዚያ ላይ የተጀመረው አብዮት ሰሜን አፍሪካ አንቀጥቅጧል፡፡ ኢትዮጵያ ከሰሜን አፍሪካ አገራት ይልቅ ለእነ ቦትስዋና ትቀርባለች፡፡ የቦትስዋና ጉዳይ ሌሎቹንም ማነቃነቁ የማይቀር ነው፡፡ ይህ ለውጡ ቅርብ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አይቀርም፡፡
‹‹ቂሊንጦም ገደብ አለብኝ›› አብርሃ ደስታ



አሁን ደህና ነኝ፡፡ ማዕከላዊ ምርመራ ማዕከል ሳለሁ ጨጓራ በጣም ያመኝ ነበር፡፡ እዛ ያለው ምግብ ነበር ያሳመመኝ፡፡ ከሰማያዊ ወጣቶች ምግብ ከውጭ መምጣት ከጀመረ ወዲህ ተሽሎኛል፡፡ አሁንም ቂሊንጦ እየመጡ እየጠየቁን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሰማያዊ ወጣቶችን እጅግ በጣም አመሰግናለሁ በሉልኝ፡፡

እዚህ እስር ላይ ያለን ሰዎች ከውጭ ምን መረጃ አለ የሚለውን ነው የምንፈልገው፡፡ አሁን ወደእናንተ ስመጣ ጎብኝ ይፈልገኛል ብዬ የእስር ቤቱን ተወካይ አስፈቅጄ ነው የመጣሁት፡፡ ገደብ አለብኝ፡፡ እኔ እና በእኛ መዝገብ አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ዘላለም ወርቃገኘሁ ጠያቂ ሲመጣ ለኃላፊዎች በጎብኝዎቻችን እንደተፈለግን ሳንናገር መውጣት እንደማንችል ተነግሮናል፡፡

‹‹ስለእኔ የእስር ጉዳይ ማሰብ አልፈልግም›› አንዱዓለም አራጌ
እኔ ለሀገሬና ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሆን የምፈልገው መልካም ነገር መቼ ይፈጸማል የሚለው እንጂ እኔ መቼ ከእስር እወጣለሁ የሚለው አሳስቦኝ አያውቅም፡፡ ሰላማዊ ትግል በባህሪው ውጤቱ በጎ ነው፡፡ እኔና መሰሎቼ በሰላማዊ ትግል ነው የምናምነው፡፡ በዚህ የትግል ስልት ደግሞ ለውጥ ሲመጣ ማየት እሻለሁ፡፡ ስለእኔ የእስር ጉዳይ ማሰብ አልፈልግም፡፡ በጋራ ቤታችን ኢትዮጵያ መልካም ነገሮች እንዲሆኑ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ነው የእኔ ምኞት!
‹‹እኛ ነጻ የምንወጣው የተባበርን ዕለት ነው›› የሺዋስ አሰፋ

በማዕከላዊ ያሳለፍነው ጊዜ ዘግናኝ ነው፡፡ በተለይ 3 ወር ተኩል የቆየንበት ሳይበሪያ የሚባል ቦታ በረዶ ቤት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ድብደባው አለ፡፡ ማዕከላዊ ውስጥ ምርመራ፣ ህክምና፣ እስረኛ አስተዳደር፣ ጥበቃና የቢሮ አስተዳደር የሚባሉ አምስት ክፍሎች አሉ፡፡ ማዕከላዊ ውስጥ ድብደባ ይፈጽማሉ፣ ሰብአዊ መብት ይጥሳሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በምርመራ ወቅት የምንደበደበው በሚስጥር ነው፡፡ ከአምስቱ ክፍል ውስጥ በአንዱ የሚሰራ መደብደባችን አሊያም የሆነ ችግር እንደተፈጠረብን ሲሰማ መረጃው ወደውጭ ይወጣል፡፡ ማዕከላዊም ቢሆን ጨካኝ ሰዎች እንዳሉት ሁሉ ጥቂትም ቢሆኑ መልካም ሰዎች አሉበት፡፡

የመርማሪዎቹ ሁኔታ ግን የሚገርም ነው፡፡ እነሱ የያዙኝ ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት አለህ ብለው ነው፡፡ ምርመራው ግን የሰማያዊ ፓርቲ የገንዘብ ምንጭ ከየት ነው? ጠንካራ ቢሮ ያላችሁ የት ነው? ጠንካራ አባልና አመራራችሁ የትኛው ነው? የሚል ነው፡፡ በምርመራ ወቅት ሳልታሰር የግንቦት ሰባትን ተቃውመው እንደሚጽፉ የማውቃቸው ሰዎች ሳይቀር ‹‹የግንቦት ሰባትን ጽሁፍ ልከውልሃል!›› ተብያለሁ፡፡

ሰው ገለዋል፣ ሰርቀዋል ....እየተባሉ ማዕከላዊ የታሰሩ ሰዎች አሉ፡፡ እነሱና ሌሎች ታሳሪዎች ቃላቸው ከክስ መዝገባቸው ጋር ይያያዛል፡፡ የእኛ ግን የሚረባ ነገር ስላላገኙበት ሊያያይዙልን አልቻሉም፡፡ በጣም የሚገርመው እኛ ተዘግቶብን ስንውል ሌሎቹ (በስርቆትና በመሳሰሉት የታሰሩት) መውጣት መግባት ይችላሉ፡፡ እንደኛ በረዶ ቤትም አይታጎሩም፡፡

እኛ የታሰርነው ለሌላ ሰውም ብለን አይደለም፡፡ እኛ የታሰርነው ለራሳችን ነጻነት ነው፡፡ ስለሆነም ምንም የሚያስፈራን ነገር የለም፡፡

ውጭ የምንሰማው እንቅስቃሴ ደስ ይላል፡፡ ዳያስፖራው እንያደረገ ያለውን አንዳንድ እንቅስቃሴ እንሰማለን፡፡ በተለይ 9 ፓርቲዎች በትብብር ለመስራት መስማማታቸው ስለሰማሁ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ለመስራት ያቀዱትም ደስ ያሰኛል፡፡ እኛ ነጻ የምንወጣው የተባበርን ዕለት ነው፡፡ ከታሰርን ጀምሮ ከጎናችን ለቆመው የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡
‹‹መሰባሰብ አለብን›› ሀብታሙ አያሌው
ማዕከላዊ የነበረን ቆይታ ዘግናኝ ነበር፡፡ የታሰርነው በጣም ቅዝቃዜ ካለው ቤት ነው፡፡ ጠዋት 11 ሰዓት ለጥቂት ጊዜ ወጥተን ማታ እንደገና ይከፈትልንና እንደገና እንገባለን፡፡ በተለይ እኔ ህመም ነበረብኝ፡፡ ብነግራቸው ሊሰሙኝ አልቻሉም፡፡ እየቆየ በጣም በረታብኝ፡፡ በጣም ታምሜ ነበር፡፡ በምርመራ ወቅት የሚደረገው በጣም ያሳዝናል፡፡ እነሱ የከሰሱኝና የሚመረምሩት የተለያየ ነው፡፡

አብዛኛው ክስ የተነሳብኝ ከኢሳት ጋር ግንኙነት በማድረግ ስርዓቱን ለመገልበጥ የሚል ነው፡፡ ኢሳት ሚዲያ ነው፡፡ እኔ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥቼ አውቃለሁ፡፡ ከዘመኑ ካሴ ጋር አለህ የተባልኩት ግንኙነት የሚገርም ነው፡፡ ከፓልቶክ የወሰዱት ንግግር ነው፡፡ በሌላ ጊዜ የተጻፈ ብቻ ሳይሆን ድምጽም ያሰሙ ነበር፡፡ የእኔን አላሰሙም፡፡ የሚገርመው ከዘመነ ጋር ተገናኘህ የተባልኩት በግንቦት 2004 ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዚህም ወቅት ቢሆን እሱን አልከሰሱትም፡፡ እኔን የከሰሱኝ በአንድነት የህዝብ ግንኙነት ሆኖ የግንቦት ሰባትን አላማ ለማሳካት የሚል ነው፡፡ የሚያሳዝነው በዚህ ወቅት እኔ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ነው የነበርኩት፡፡
በጣም የሚያሳዝነው በእኛ ላይ ያቀረቡት ክስ አይደለም፡፡ በክሱ ላይ አንድነት፣ ሰማያዊና አረና የጸረ ሽብር፣ የሚዲያ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የመሳሰሉትን አዋጆችና ህጎች ስለማይቀበሉ ህገ ወጦች ተደርገው ተወስደዋል፡፡ እኛ ከእነዚህ አመራሮቻቸው መካከል እየተባልን ነው ድምዳሜው የተሰጠብን፡፡ ሌላም ሊያጠቁት የሚፈልጉት ሰው አለ ማለት ነው፡፡

ተቃዋሚዎች ተባብረው ለመስራት እየጣሩ እንደሆነ ሰምቻለሁ ደስ ብሎኛል፡፡ መንገዳችን አንድ ነው፡፡ መሰባሰብ አለብን፡፡ አንድነትም ወደ ስብስቡ እንደሚመጣ ተስፋ አለኝ፡፡ ተሰባስበን ስንሰራ ነው በደሉን ልናስቆመው የምንችለው፡፡

በስተመጨረሻም ከታሰርንበት ጊዜ ጀምሮ ከጎናችን ለቆመው አገር ውጥም ሆነ በውጭ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና ላቀርብ እፈልጋለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment