ሜይ 17ን ብመኘው?
የኖርወይ ሕዝብ ሕገመንግሥታቸውን ያወጁት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1814 ማለትም የዛሬ
200 ዓመት ነበር።
አንድ መቶ አስራ ሁለት የአገሪቱ ታላላቅ ሰዎች በሀገር ፍቅር ቀናኢ ስሜት በመነሣሣት ሕገ መንግስቱን
በዘመኑ ነባራዊ ሐቅ ላይ በመመሥረት እንዲሁም ጊዜ በፈቀደው ጥበብና ቋንቋ በአስደናቂ ክህሎት
አረቀቁት ።
ታዲያ ይህ ሕገ መንግስት
በወቅቱ የነበሩትን ባለስልጣናት የሚያገለግል ሳይሆን የሐገሪቱን ሕዝብን ማዕከል ያደረገና ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዲሞክራሴያዊ
ሕጎች ጋራ የተጣጣመ ረቂቅ ነበር ።
ይህ ሕገ መንግሥት በዚያን ጊዜ ተቀባይነትን አግኝቶ በከፍተኛ አድናቆት ቢፀድቅም ቅሉ፤እንደ ማንኛውም
ሰው ሰራሽ ሕገመንግሥት ሁሉ፥ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄና ፍላጎት መሠረት በማድረግ እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ የሆኑ መሻሻሎች ተደርገውበታል።
ለዚህ እውነታ ዋቤ መጥቀስ ካስፈለገም በመጀመሪያው ረቂቅ ላይ እምብዛም ትኩረት ያልተሰጣቸው የሴቶችና የህፃናት መብት መከበርን
የመሳሰሉት በጎላ ሁኔታ ተካተውበት ሕዝባዊነቱ የበለጠ ለዓለም ሁሉ ጎልቶ እንዲያንጸባርቅ ተደርጎአል።
ታዲያ ይህ ሁሉ መሻሻልና
ለውጥ የሆነው በሕዝብ ፈቃድ ብቻ እንጂ በማንም ግላዊ ውሳኔ አይደአለም።