በኩዌይት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው
መጋቢት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ውጥረቱ የተጀመረው አንዲት ኢትዮጵያዊት አንድ የአገሪቱን ባለስልጣን ልጅ መግደሉዋን ተከትሎ ነው። ኢትዮጵያዊቷ ግድያውን የፈጸመችበትን ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ ባይቻልም፣ ገዳዩዋን በቅርብ እናውቃለን ከሚሉ ወገኖች የተገኘው መረጃ በቂም በቀል ተብሎ የተደረገ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ይገልጻሉ። ከሶስት አመት በፊት ወደ ኩዌት የገባችው ወጣት በመጀመሪያው ወር በአሰሪዋ ልጅ መደፈሩዋን ለመበቀል በሚል የባለስልጣኑን ልጅ ለመግደል እንደተነሳሳች መግለጿን ኢትዮጵያውያን ይናገራሉ።
የኩዌት መንግስት ስለ ግድያው መንስኤ እስካሁን በኦፌሴል ያሳወቀው ነገር የለም። ይሁን እንጅ የኩዌት የፓርላማ አባላትና አንዳንድ ባለስልጣናት ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው እንዲወጡ እየወተወቱ ነው።
የሟች አክስት የሆነች አንዲት ማንነቱዋ ያልተገለጸ አሰሪ ከአራት ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች መካከል እጣ በማውጣት አንደኛዋን ኢትዮጵያዊት በማረድ የአክስቷን ልጅ ሞት መበቀሉዋን ኢትዮጵያውያን በፎቶ ግራፍ አስደግፈው ለኢሳት የላኩት መረጃ ያሳያል።
ኢሳት ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ከቤት ለመውጣት እንዳልቻሉ፣ ከቤት ቢወጡ ተይዘው እንደሚታሰሩ ወይም የበቀል ሰለባ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በፍጥነት ደርሶ አሁን የተፈጠረውን ውጥረት እንዲያረግብም ኢትዮጵያውያን ተማጽነዋል። በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁኔታውን በንቃት እንዲከታተሉት ጥሪ አቅርበዋል። ኢሳት የኩዌት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሰካም።
No comments:
Post a Comment