የቁልቁለት መንገድ
በማስመሰል ታጥሮ መሆን በጠፋበት ምን አገባኝ የሚል በተከማቸበት የባይተዋር መንፈስ ከሞላ ባገሩ
ዘመኑን ማወቂያ ይሄ ነው ሚስጥሩ
ይሄን ጊዜ ጠርጥር እንደጠፋ ዘሩ፡፡
(ገጣሚ ደምሰው መርሻ/ያልታተመ)
ጋዜጠኛ
ተመስገን ደሳለኝ
አዎን፣ ገጣሚ ደምሰው እንዳለው እኔም በዚህ ዘመን “ዘሩ እንደጠፋ” አሊያም ሊጠፋ እንደተቃረበ እጠረጥራለሁ፡፡ ስለምን? ቢሉ ...በኢትዮጵያችን ለህሊናው፣ ለሕዝብና ለሀገሩ የሚቆረቆር፣ የእውነት ተሟጋችና የሞራል ልዕልናን የተቀዳጀ ሙሉ ሰው ፈልጎ ማግኘት እጅግ አተካች ሆኗልና፡፡የግል ጥቅም አሳዳጅ፣
አፋሽ-አጎንባሽ በሞላበት፣ እንደ ቴዎድሮስ ለሀገር ቤዛ መሆን፤ እንደ ግርማሜዎቹ እና ወርቅነህ የራስን ምቾት ወዲያ ጥሎ በጠገበ ሆድ ከወገን ጋር መራብና ከጎኑ መቆም፤ እንደ አቶ ሽፈራው ደሳለኝ አስፈሪ ሞት ከከበበው ሸለቆ ውስጥ በህይወት ለመውጣት ሲባል የጠላትን ጫማ ከመላስና ያላመኑበትን ተናግሮ ምህረት ከመጠየቅ ይልቅ በድፍረት ሞትን ፊት ለፊት መጋፈጥ ወይም ግንባርን ለአረር መስጠት እንደ ተረታ-ተረት ከተቆጠረ ዘመናት አልፏል (አቶ ሽፈራው ደሳለኝ ማን ናቸው? ለሚለኝ አንባቢዬ ‹‹የታኀሣሡ ግርግር እና መዘዙ›› የተሰኘውን የብርሃኑ አስረስ መጽሐፍ ገፅ 302ን እንዲያነብ እጋብዘዋለሁ) አሊያም ደግሞ የሰው ዘር በመሆን ብቻ የሚገኘውን የሞራል ልዕልና ከትውልድና ሀገር ጥቅም አኳያ ለማጠየቅ በዚህ አውድ ለማነሳው ተጠየቅ በአንፅሮ ለማፍታታት ይጠቅመኝ ዘንድ እኔው ራሴ እዚሁ ጠቅሼው አልፋለሁ፡፡
የመጽሐፉ ደራሲ ‹‹በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጊዜ የድጋፍ ንግግር አድርጋችኋል በማለት በመንግስት ተይዘው ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ከተላኩት አንዱ የሆኑት...›› ብለው ከአቶ ሽፈራው ደሳለኝ ጋር ከአስተዋወቁን በኋላ እንዲህ በማለት ትርክታቸውን ይቀጥላሉ፡- ‹‹...አቶ ሽፈራው ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ተልከው ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ የእምነት ክህደት ቃል ሲጠየቁ ዳኛው ‹ሠርተሃል ለተባለው ወንጀል ጥፋተኛ ነህ፣ አይደለህም?› ይላቸዋል፡፡ ‹የቱን ወንጀል?› ሲሉ አቶ ሽፈራው ዳኛውን ይጠይቃሉ፡፡ ዳኛው አቶ ሽፈራው ሠርተዋል የተባለውን የወንጀል ቃል ሊናገሩት አልወደዱም አልደፈሩምምና ‹አንተ የሠራኸውን?› ብለው ጠየቁ፡፡ አቶ ሽፈራው ‹እስቲ ወንጀል የተባለው ይነበብልኝ› ብለው አጥብቀው ይጠይቃሉ፡፡ ይሄን ጊዜ ዳኛው ሳይወዱ ‹ይህን ጣሳ እግዚአብሔር ገላገለን፣ አወረደልን ማለትህን፤ ...ለዚህ ጥፋተኛ ነህ አይደለህም?› ይሏቸዋል፡፡ ‹የለም ተስተካክሎ ይጻፍልኝና እምነት ክህደቴን ልናገር› ይላሉ፡፡ ‹የለም በዚህ ላይ ጥፋተኛ ነኝ በል› ይሏቸዋል፡፡ ‹ትክክለኛ ቃሌ ይጻፍና ነው እንጂ እንዲሁ ጥፋተኛ ነኝ፤ አይደለሁም፤ አልልም› ብለው ይመልሳሉ፡፡ ‹እሺ ምን ተብሎ ይስተካከል› ሲሏቸው፤ ‹ይህን የበሰበሰ የተጠረማመሰ አሮጌ ጣሳ እግዚአብሔር ገላገለን ነው ያልኩት› ሲሉ ዳኞቹ የተባለውን አልሰማንም ለማለት ራሳቸውን ጠረጴዛ ስር አግብተው ተደበቁ፡፡››
በዚህ ዘመን ራሳቸውን ጠረጴዛ ስር አግብተው እንደ ሰጎን አንገታቸውን ቀብረው በፍርሃት የሚኖሩ አድር፣ እበላ-ባይ፣ ፈሪ ሰዎች የአቶ ሽፈራውን ባመኑበት መቆም እንደ አጎል ጀብደኝነትና ሞኝነት ቢቆጥሩት አስገራሚ አይሆንም፡፡ የሆነው ሆኖ እንደ ብልህነት አሊያም ብልጥነት ተደርጎ የሚወሰደውን የአድርባይነት ‹‹ስልት›› ለማሳየት አንዲት ሀገርኛ ምሳሌ እዚህ ጋ ለንፅፅር ላቅርብና እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ለራሴ ጽሑፍ ‹‹F›› ከመስጠቴ በፊት ወደ አጀንዳዬ ልዝለቅ፡፡
ታሪኩ ዝናው በስፋት የናኘ ሽፍታ የመሸገበትን (ግዛቱ ያደረገ) ጥቅጥቅ ያለ ጫካ አቋርጦ ስለሚያልፍ መንገደኛ ገጠመኝ ነው፡፡ መንገደኛው ለሰዓታት ከተጓዘ በኋላ ድንገት ሽፍታው እጅ ይወድቅና ስንቅ የቋጠረበትን ስልቻ ጨምሮ ከላይ እስከታች ይበረበራል፤ ሆኖም ሰባራ ሳንቲም ሊያገኝበት ባለመቻሉ ከመጠን በላይ የተበሳጨው አያ ሽፍታ ሆዬ ንዴቱን ለማብረድ ሲል ‹‹ውዳሴ ዜማ አቅርብልኝ!›› በማለት ቀጭን ትዕዛዝ ይሰጠዋል፤ በፍርሃት ነፍሱ እጉሮሮው የተወተፈችበት መንገደኛም ተንፈስ ብሎ ለመረጋጋት እየሞከረ እንዲህ ሲል አቀነቀነለት ይባላል፡-
‹‹አይኑ የተኳለ ጠላት የሚጋረፍ
ጠብ-መንጃ ገስጋሽ ጉብታ ተሻግሮ ከዘብጥ የሚናደፍ
እንደሚካኤል ነህ ጠላትህም አይተርፍ!››
እነሆም የሀገሬ ምድር እንዲህ ባሉ ሀሞተ-ቢስ አወዳሾችና አስመሳዮች ተጥለቅልቃ እጆቿን ወደ ሰማይ ከዘረጋች (ሱባኤ ለመግባት) ሰነበተች፡፡ በርግጥም ከብዙሀኑ በተሻለ ማንሰላሰል ይሳናቸዋል ተብለው የማይታሰቡ ‹‹ምሁራን››ም ሆኑ ‹‹መንፈሳዊ››ነታቸው የበዛ የኃይማኖት መሪዎች በግል ጥቅመኝነት ታውረው ከስርዓቱ ጋር እጅና ጓንት በመሆን የጭቆና አገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም በሀሰት መስካሪነት የቅጥፈት ምላሳቸውን ሲያንበለብሉ መስማት ‹እግዚኦ› የሚያስብል አስደንጋጭ መናፍቅነት መሆኑ ቀርቶ እንደ ተራ ነጋዴ ንግግር፣ ተራ የዕለት ተዕለት አጋጣሚ ከሆነ ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ ‹‹መንፈሳዊያን›› አባቶች በተከበረው ቤተ-መቅደስ ምኩራብ ላይ ከመእምናኑ ፊት ለፊት ቆመው ቃየልን ‹‹አቤል››፣ በርባንን ‹‹መሲህ›› በማለት ሲሰብኩም ለአመል እንኳ ድንቅፍ አያደርጋቸውም፤ ከግላዊ ጥቅማቸው አሻግረው የግፉአንን የስቃይ እሮሮ ማድመጥም ሆነ ለሌላው ማሳወቅ ጭራሹንም አይሞክሩትም፡፡ ‹‹ምሁራን›› ተብዬዎቹም አርቲስት ሰለሞን ተካልኝ ‹‹ውበት ከቅንድቡ የሚፈስ›› እንዲል፤ ‹አይኑ የተኳለ› እያሉ በሕፃናት ደም ሳይቀር የጨቀየውን ኢህአዴግ መራሹን መንግስት እንዴት እንዴት ‹ብፁእ› አድርገው የውዳሴ ከበሮ ሲመቱለት እንደሚያድሩ እዚህ ጋ ዘርዝሮ ለማቅረብ ማሰብ አባይን በጭልፋ አጋብቶ ለመጨረስ እንደመሞከር ያለ ዕብደት ያስቆጥራል፡፡
ወጣም ወረደ እንዲህ አይነቱ የሞራል ዝቅጠት በትላንት ወይም በዛሬ የእድሜ ገደብ የሚለካ አለመሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል፤ ምክንያቱም በነገሥታቱ የአገዛዝ ዘመን የጀመረና በጣሊያን የአምስት ዓመቱ የወረራ ወቅት እንደወረርሽኝ የተስፋፋ ስለመሆኑ በቂ ማሳያዎች አሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ‹‹ሀገር›› ለተሰኘ ማህተም መስዋዕት የሆኑትን አቡነ ጴጥሮስን የመሳሰሉ ታሪክ በታላቅ አክብሮት የሚዘክራቸውን ቀዳማይ አባቶችና እናቶችን ሳንዘነጋ ነው፡፡ እናም የሩቁን ትተን ከ1983ቱ የመንግስት ለውጥ ወዲህ ያለውን እንኳ ብንመለከት ይህን መሰሉ ክስረት ዙሪያችንን ከቦ ሊውጠን የቀረው ስንዝር ታህል ርቀት ብቻ መሆኑን ለመረዳት የማሕበራዊ ሳይንስ ምሁራን ትንታኔን ማገላበጥ አይጠይቅም፡፡ ያኔ ገና በለውጡ ማግስት ህወሓት እና ሻዕቢያ በአንድ አንቀልባ ካልታዘልን በሚሉበት የ‹‹ጫጉላ›› ዘመን፣ ከኤርትራ ምድር የወርቅ ጥርሳቸው ሳይቀር በጭካኔ ወልቆ ባዶ እጃቸውን የተባረሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ በጉምቱው ምሁር ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ የተመራው አጣሪ ቡድን ‹‹ውሸት ነው! ይህ አይነቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኤርትራ ይኖሩ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ላይ አልተፈፀመም!!›› በማለት አይኑን በጨው አጥቦ በድፍረት ሲያስተባብል፣ አንጀታችን እያረረ ‹‹ይሁና!›› ብለን በትዝብት ማለፋችን እውነት ቢሆንም፤ የዝምታችን ውስጠ-መልዕክት ያልገባው ፕሮፌሰሩ ግን ያረረው አንጀታችን ይበልጥ እርር ይል ዘንድ በተለመደው ቅጥፈቱ ታላቁ የዐድዋ ድል ባለቤትነትን ከሀገር ከፍታ፣ ቁልቁል ወደ ጎጥ ለማውረድ ያልፈነቀለው ቋጥኝ፣ ያልማሰው ስር አልነበረም (በነገራችን ላይ ህወሓት ዛሬም ከዐድዋ ድል ጀግኖች ጋር ጥቁር ደም እንደተቃባ በግላጭ የሚያመላክተው በዘንድሮው 118ኛው ክብረ በዓል ላይ የተስተዋለው አሳፋሪ ትእይንት ነው፡፡ ይኸውም በታሪካዊቷ ዐድዋ ከተማ በሚገኘው ሶሎዳ ተራራ ስር ‹ድሉን ለመዘከር› ከተሰቀሉት የእቴጌ ጣይቱ፣ የራስ አሉላ አባነጋ፣ የባልቻ አባነፍሶ እና የባሻ አውዓሎም ግዙፍ ምስሎች መሀል የተሸናፊው ሀገር ህዝብ ሳይቀር በድሉ ዕለት ሮማ በተሰኘው አደባባዩ ‹‹ቪቫ ምኒሊክ›› እያለ በታላቅ ጩኸት ያወደሰው የታላቁ ንጉሠ ነገሥት ምስል አለመካተቱ ነው፡፡ ...መቼም ይህ ለምን ሆነ? ብለን የክልሉን አስተዳዳሪ ጓድ አባይ ወልዱን ብንጠይቀው ‹‹በጦርነቱ ወቅት ምኒሊክ መሸሽ ጀምሮ ነበር›› የሚለውን ዝነኛ ህወሓታዊ ትርክት ገልብጦ፣ ‹‹በስራ መደራረብ በተፈጠረ ስህተት ነው›› ብሎ በክፍለ ዘመኑ ታላቅ ሽርደዳ አንጀታችንን ይበልጥ ድብን እንደሚያደርገው ቅንጣት ታህል አትጠራጠሩ)
ለማንኛውም እንደ ፕሮፌሰር እንድሪያስ ያሉ በድሃው ሕዝብ ጥሪት የከፍተኛ ደረጃ የትምህርት ዕድል ማግኘት የቻሉ በርካታ እበላ-ባይ ‹‹ምሁራን›› ስርዓቱ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም የሚያምታታበትን ‹‹የሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት›› የፈረንጅ ጥናቶችን በጥራዝ- ነጠቅነት እያጣቀሱ ምክንያታዊ መስለው ሊያሳምኑን በከንቱ ብዙ ደክመዋል፡፡ በአናቱም የመከላከያ ሠራዊቱ ለባዕድ ሀገር ጥቅም ሲባል ሶማሊያን በወረረበት ወቅት አንዳንድ የዩንቨርስቲ መምህራን እና ‹‹የፖለቲካ ተንታኞች›› በመሬት ያለውን ተጨባጭ እውነታ ይሁነኝ ብለው ወደጎን ገፍተው አገዛዙ ቀን ከሌት ‹‹እመኑኝ!›› በሚል ጩኸት ያሰለቸንን ሰበብ፣ በጥናት እንደተረጋገጠ አስመስለው ለመተንተን ያደርጉት የነበረው እሽቅድምድም ሁሌም በሀዘን የምናስታውሰው ነው፡፡
የኃይማኖት መሪዎችም ምንም እንኳ በነቢብ የአገልግሎታቸው ዋጋ በፈጣሪ መንግስት መሆኑን ደጋግመው ቢነግሩንም፣ በሀልዮ የሚታየው የአሸርጋጅነት ግብራቸው ግን ምድራዊውን ጨቋኝ ስርዓት ደግፎ የሚይዝ ምሰሶና አቅፎ የሚያሞቅ ክንድ ከሆነ በርካታ አስርታት ተቆጥረዋል፡፡ የእስልምና እምነት የበላይ ወሳኝ አካል የሆነው መጅሊስ መእምናኑ ያነሱት ፍትሃዊው የመብት ጥያቄ ተቀልብሶ፣ ሕዝባዊ ውክልና የተሰጣቸው የኮሚቴ አባላት ለአስከፊው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የተዳረጉበትን መንግስታዊ ሽብርተኝነት ለመሸፋፈን ከመተባበርም አልፎ ቅዱስ ቁራንን አዛብቶ እስከመጥቀስ መድረሱ በትዝብት ያሳለፍነው የትላንት ኩነት ነው፡፡ የክርስትና እምነት መሪዎችም በተመሳሳይ ሁናቴ የስርዓቱን የጭካኔ እርምጃዎች እንደ ቅዱስ ተግባር ለማፅደቅ ያልረጩት ጠበል፣ ያልጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አልነበረም፡፡ ሌላ ሌላውን እንኳን ትተን በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው የኦሮሚያ ክልል አስተዳዳሪ የአለማየሁ አቱምሳ ስርዓተ ቀብር ላይ ፓትርያርክ ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ‹ዲሞክራሲን ለማስፈን መስዋዕትነት የከፈለ፤ ሩጫውን የጨረሰ፤ ተጋድሎውን በብቃትና በንቃት የተወጣ...› እያሉ አፋቸውን ሞልተው የምስክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ ሀፍረት ብሎ ነገር ለቅፅበት እንኳን ዝር
አላለባቸውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በሰውየው ህልፈት እጃቸው እንዳለበት የሀሜት ወሬ የሚናፈስባቸው እነዚያ ጲላጦሳውያን ጓዶቹ እንዳሻቸው ቢያንቆለጳጵሱት መቼስ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው ብሎ በቸልታ ማለፍ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሰማዩን መንግስት ብቻ ያገለግሉ ዘንድ በቃሉ እንዲመላለሱ ግድ የሚላቸው ‹‹መንፈሳውያን››፣ እንዲያ የገዛ ወገኑን ‹‹ኦነግ!›› በሚል የሀሰት ውንጀላ በጥይት ሲደበድብና ሲያስደበድብ፤ መከራን በሕዝብ ላይ እንደምርጊት ሲለስን፤ አምባገነን ስርዓቱን በታማኝነት ሲያገለግል... ያለፈን ሰው ‹‹ዲሞክራት›› እያሉ በአደባባይ ማወደስ በቤተ-ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ራሱ የተነቀፈውን ለእግዚአብሔርና ለቄሳር ዕኩል መገዛትን እንደትክክለኛ ተግባር አምኖ መቀበል ነው ወደሚል ጠርዝ መገፋታችን አይቀርም፡፡
በግልባጩ በሁሉም እምነት ያሉ ‹‹መንፈሳዊ›› መሪዎች ስርዓቱ በድህረ-ምርጫ 97ም ሆነ በተከታዮቹ ዓመታት የተቃዋሚ ፓርቲ የአመራር አባላትን እና ጋዜጠኞችን እንደ ጥጃ እያሰረ በግፍ ሲያሰቃይ ድርጊቱን ለመንቀፍም ሆነ ዘላቂ ዕርቅ እንዲወርድ ለመማለድ አንዳች ሙከራ አለማድረጋቸው በታሪክ ጥቁር መዝገብ በጉልህ ቀለማት ሰፍሮ የሚኖር ሀጢያታቸው ነው (የቅንጅት እስረኞችን ለማስፈታት የተሄደበት የ‹‹ሽምግልና›› መንገድ የአቶ መለስ ዜናዊ ቧልት ስለመሆኑ ከቶም ማንም ሊጠራጠረው አይችልምና እዚህ መጥቀሱ አስፈላጊ አይመስለኝም)
ሌላው የማሕበረሰባችን የሞራል እሴት በእጅጉ መዝቀጡን የሚያስረግጥልን ብዙሀኑ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በተዘፈነበት ለመደነስ፣ በተደገሰበት አሳላፊ ለመሆን የሚያደርጉትን መገፋፋት ስናስተውል ነው፡፡ ስርዓቱ ከሚያራምደው ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ›› ርዕዮተ- አለም የተቀመረውን ‹‹ፌደራሊዝም አወቃቀር››ን ተንተርሶ ሀገሪቱን በዘውግ ከፋፍሎ እና በሕዝብ መካከል የጥርጣሬ መንፈስ አንብሮ የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሙን በግጥምና ዜማ ማወደስ የእህል-ውሃ ጥያቄ ካደረጉት በርካታ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ እንዲህ አይነት የሙዚቃ ስራ በአንዳንድ ክልሎች መሬት የሚያሸልም ፈጣን አዋጪ አድርባይትመንት (ኢንቨስትመንት ላለማለት ነው) እስከ መሆን መድረሱ ከታፊና ነጋዴ አርቲስቶች በዘውጉ ዙሪያ ይረባረቡ ዘንድ ታላቅ ልማታዊ አብነት ሆኗቸዋል፡፡ ይህ ሁናቴም በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብን የንፁሃን መታጣት ከድንጋይ ወገራ የታደጋትን የኦሪቷ ዘማዊት ከማስመሰልም አልፎ እንደ ነገሥታቱ ዘመን የአዝማሪ ጨዋታ፤ የቤተ- መንግስቱ መዝናኛ እና አጀንዳ ማራገቢያነት እስከ መሆን ሞዴል ተሸላሚ አድርጓታል፡፡ ይሁንና ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ቴዎድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮን) የመሳሰሉ መክሊታቸውን እንደ ጉሊት ሽንኩርት ለሽያጭ ያላቀረቡ ከያኒያን፣ ደራሲያን፣ ገጣሚያን... የመኖራቸውን እውነታ ሳንዘነጋ፤ ሀገሪቱ ‹‹ሰው አይብቀልብሽ!›› ተብላ የተረገመች እስኪመስል ድረስ ብሔራዊ ጥቅም፣ ህሊና፣ ሞራል፣ እውነት የረከሱበትና የተዋረዱበት ዘመን ላይ መድረሷን የሚያስረግጡልን በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በብአዴኑ ካሳ ተክለብርሃን ፊት-አውራሪነት የሶማሌ ክልልን የጎበኙት አርቲስቶቻችን፣ ገና ድሮ ጆርጅ ኦርዌል ‹‹Animal Farm›› ብሎ በሰየመው መጽሐፉ ‹‹አራት እግር ጥሩ፤ ሁለት እግር መጥፎ›› እያሉ በመንጫጫት ስብሰባን ለመረበሽና ተቃውሞን ለማጨናገፍ አሳማው ናፖሊዮን እንዳሰለጠናቸው አይነት በጎች፤ ኢህአዴግ በጎጥ የካፋፈለውን ሕዝብ ‹‹በታሪኩ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን አንድ ሆኗል!!›› በማለት በሬ ወለደ የሀሰት ምስክርነታቸውን አምነን እንድንቀበል ለማድረግ ለሳምንታት ተንጫጭተው ሊያደነቁሩን ሞክረዋል፡፡ እነዚህ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የክልሉ ነዋሪዎች ገና ዛሬ (በኢህአዴግ እፁብ ድንቅ እና ፍትሀዊ አስተዳደር) ኢትዮጵያዊነት እንደተሰማቸው፤ ገና ዛሬ በፍቃደኝነት ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ አስመስለው ለማሳመን የሄዱበት የቁልቁለት መንገድ አጥንት ድረስ በሚዘልቅ ሀዘን እንዳኮራመተን እነርሱም ይጠፋቸዋል ብዬ አላስብም፡፡ ጉዳዩ ሆድ ሌላ፣ እውነት ሌላ ሆኖባቸው እንጂ፡፡ ግና፣ የቄሳሩ ጲላጦስም ‹‹እውነት ምንድር ነች?›› እንዲል፣ እውነት ለእነርሱ ዋጋዋ ስንት ነው? መቼም ከእውነት ይልቅ ግድ የሚሰጣቸው የሆድ ነገር ነው፤ እበላ አዳሪዎች ናቸውና፡፡
በጥቅሉ በኢትዮጵያችን ከምሁር እስከ ተርታው፤ ከጳጳሳት (ፓስተራት) እና ሼሆች እስከ መናፍቃውያን፤ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ፤ ከጄነራል እስከ ወታደር፤ ከከያኒ እስከ ጽሑፍ ገልባጭ፤ ከቱጃር እስከ ጥሮ-ግሮ አዳሪ፤ ከመምህር እስከ ተማሪ... ስር የሰደደ አድርባይነት እና የሞራል ክስረት ለመንሰራፋቱ አይነተኛ ማሳያው አምባገነኑ ኢህአዴግ እንዲህ ሚሊዮኖችን ረግጦ እየጨፈለቀ፣ አስሮ እያንገላታ፣ ከሀገር እያሰደደና እየገደለ... ከሁለት አስርት በላይ መቆየት የመቻሉ ምስጢር ነው፡፡ ግና፣ የሕዝብን መከራ በማራዘም ኪስን ማደለብ፣ ግላዊ ፍላጎትን ማርካት ሁሌም አትራፊ ሊሆን እንደማይቻል መዘንጋት የለበትም፡፡ ማን ነበር ‹የተከፋፋለና አድርባይ ሕዝብን ከጭቆና ማላቀቅ፣ ሰማይን የማረስ ያህል አዳጋች ነው!› ያለው?
አዎን፣ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ በጉልበታም ስርዓታት የጭካኔ መዳፍም ሆነ በግላዊ ጥቅመኝነት እየተናዱ የመጡት የባህል እና የሞራል እሴቶች ትውልዱን ዛሬ ላይ ለደረሰበት አስከፊ ማሕበራዊ ቀውስ መዳረጋቸው አሌ የማይባል ነው፡፡ ርግጥ ነው የችግሩ ስፋትና ጥልቀት እንደ ስርዓቱ የፖለቲካ ፍልስፍና በዘውግ የተከፋፈለ አይደለም፤ ብዙሀን እና ህዳጣን የሚል መስፈርትንም የተከተለ አይደለም፤ ኃይማኖታዊ መለያም የለውም፤ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አለቅጥ መንሰራፋቱ በግላጭ ይታያልና፡፡ ይህም ነው መፍትሔውን ስር ነቀል የማሕበራዊ አብዮት (ለውጥ) ብቻ እንዲሆን ያስገድደው፡፡
የቀደሙት ሁለት አብዮቶች በዋናነት ያነሷቸው የብሔር እና የመሬት ጥያቄ መክሸፋቸው (መቀልበሳቸው) ዛሬም ሶስተኛ አብዮትን የማይቀር ዕዳ አድርጎ የመውሰዱ ሁነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሥራ-አጥነት፣ ከነባሩ ባህል ማፈንገጥ፣ ሙስና፣ በሕብረተሰቡ ዘንድ አክብሮትና
3
ተሰሚነት ያላቸው ታላላቆችን አለማደመጥ፣ አድርባይነት፣ ደንታቢስነት፣ ዶሮ ሳይጮኽ ደጋግሞ መክዳት፣ የ‹‹ስቀሎ፣ ስቀሎ...›› ሀሰተኛ ድምፅ መበራከት፣ ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች እና የመሳሳሉት ትውልድና ሀገር ገዳይ ደዌዎችን ለመፈወስ ከማሕበራዊ አብዮት ያነሰ መፍትሔ እንደሌለ ከተለያዩ ሀገራት ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ኢህአዴግ በየትኛውም የዓለማችን ሀገራት የተከሰተ ሕዝባዊ አብዮት እንቅልፍ እንደሚነሳው በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ለተከታታይ ቀናት ‹‹ተንታኝ›› ጭምር በመጋበዝ፣ ምስራቅ አውሮፓ ድረስ ተጉዞ የተሳካውን የዩክሬን አብዮት ከቀለም ጋር በማያያዝ ለማውገዝ ያቀረባቸው ፕሮግራሞች የፍርሃቱ መጠን አንዱ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላል፡፡ ግና፣ እውነት እውነት እልሀለሁ በመቶ ሺህ የሚቆጠር የታጠቀ ኃይል ቢሰለፍ፣ እልፍ አእላፍ ፊርማቶሪዎች በሕዝብ መሀል ቢሰገሰጉ፣ ሚሊዮናት ካድሬዎች ሀገር-ምድሩን ቢያጥለቀልቁ፤ አገዛዛዊ ጭቆና እና ማሕበራዊ ክስረት እስካለ ድረስ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ፣ የትኛውም ምድራዊ ኃይል ሊያመክነው የማይችል አብዮት መቀጣጠሉ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡
በመጨረሻም ይህንን ጽሑፍ ጄነራል መንግስቱ ነዋይ በተለምዶ ‹‹የታሕሳስ ግርግር›› እየተባለ የሚጠራውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መክሸፍ ተከትሎ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት በሰጠው ቃል እቋጨዋለሁ፡-
‹‹...ዋ! ዋ! ዋ! ለእናንተም ለግዥአችሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀሳቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት በሚነሳበት ጊዜ የሚደርስባችሁ መዓት የሚያሳቅቅ ይሆናል፡፡››
ትንቢቱ ከ13 ዓመት በኋላ ከእጥፍ በላይ መፈፀሙን ስናስታውስ፣ በጥቅመኝነት ስሌት ከስርዓቱ ጋር ተወዳጅተው የግፉአንን የመከራ ዕድሜ የሚያራዝሙ አድርባዮችም ሆኑ የአገዛዙ ልሂቃን ሕዝቡ ‹‹ሆ!›› ብሎ በአንድነት የተነሳ ዕለት ከመዓቱ ያመልጡ ዘንድ አይቻላቸውምና ዛሬውኑ ‹ንሰሀ ግቡ!› ብሎ ማሳሰብ ግድ ይላል፡፡ ...ዋ! ዋ!! ዋ!!!
No comments:
Post a Comment