Thursday, March 7, 2013

የህወሓት/ኢህአዴግ የውስጥ ፍጥጫ፣ ዴሞክራሲን አይወልድም


የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) በአገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ ያለው አምባገነን አገዛዝ ሕዝባችንን ከዕለት ወደ ዕለት  ለከፋ ስቃይ እየዳረገው እንደሆነ በተደጋጋሚ አስገንዝቧል።  አሁን ደግሞ አምባገነኑ አገዛዝ እራሱ ሊወጣ ወደማይችልበት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እየተዘፈቀ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል።የመለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ በህወሓት/ ኢህአዴግ ውስጥ የሚታየው ግልፅ ሽኩቻና  ፍትጊያ እጅግ እየተፋጠነ መሄዱ ይህንኑ ሃቅ ያረጋግጣል።
ይህንን  ፉክክር የሚያካሂዱት የድርጂቱ አባላት በተወሰነ ደረጃ ይቀያየሩ እንጂ፣ በመሠረታዊነት ቢያንስ ሁለት ቦታ ተፋጠው የሚገኙ ቡድኖች መከሰታቸውን መገንዘብ ይቻላል።
አንዱ ቡድን ሌላውን በሙስና፣ በጎታችነት ወይም ደግሞ ህወሓትን በመክዳት… ወዘተ ይከሳል። የተወሰኑት ደግሞ በሁለቱ ካምፕ ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ከህዝብ ደብቆ ለመጓዝ እየጣሩ ቢሆንም፣ ችግሩ ግን ወደ ሕዝብ ጆሮ ደርሶ ፀሐይ ከሞቀው ውሎ አድሯል።
የዚህ ከፍፍል አንዱና ዋና ተዋናኝ የሆነው ስብሀት ነጋ ለመገናኛ ብዙሀን በቅርቡ በሰጠው መግለጫ በህወሓት/ ኢህአዴግ ውሰጥ ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌለና  ልዩነት ቢኖርም “በዴሞክራሲያዊ መንገድ” እንደሚፈታ ለመግለጽ ሞክሯል።  ይሁን እንጂ ወዲያውኑ “መለስን የሚተካ የህወሓት ሰው ለምን አልተገኘም? ለምን ሃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ ተመረጠ?” የሚል ከፍተኛ ጥያቄ በህዝቡ ውስጥ እንዳስነሳ ከትግራይ የሚተላለፈው ሬዲዮ በድንገት ሳያስበው አሰራጭቷል።

ይህ የሚያሳየው የህወሀት/ ኢህአዴግ መሪዎች አሁንም እንደ ልማዳቸው በውሰጣችው ያለውን ቀውስ ከህዝብ ደብቀው ለመቀጠል ቢፍጨረጨሩም ከቶውንም እንዳልሆነላቸውና ሽኩቻውን አጠናክረው እንደቀጠሉ መሆኑን ነው። ፍጥጫው እጅግ የከረረ ሲሆን ልዩነት መኖሩን በግልፅ የሚያምኑት ግን እንደተለመደው ጠንካራው ወገን ሌላውን የማባረር፣ የማሰርና ካስፈለገም የማጥፋት ዕቅዱን ይፋ ማድረግ ሲጀምር ነው።
በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች (ህወሓት፣ ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴን) ውስጥ የሚገኙ ሁሉ ድርጅቶቻቸውን ለረጅም ጊዜ ከተዘፈቁበት አረንቋ ውስጥ በማውጣት የሀገራችን ክብርና የህዝባችን መብት ያረጋገጠ መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ እንዲታገሉ በዚህ አጋጣሚ ሸንጎው ጥሪውን ያቀርባል።
ሸንጎው የሚሻው መሠረታዊ ለውጥን እውን በማድረግ ቂም በቀል የሌለባት፥ ሁሉንም ዜጎች እኩል የምታሰተናግድ፥ አድልዖ የሌለባት የሁሉም ዜጋ መብት የተረጋገጠባት፥ የህግ የበላይነት የሰፈነባት አንድነቷ የተጠበቀባትና ዜጎቿን ሁሉ የምታኮራ ኢትዮጵያን በጋራ እውን ማድረግ ነው።  በዚህ ተጠቃሚ የሚሆነው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው።
ይህን ዓይነት ሀገርንና ህዝብን የሚጠቅም ለውጥ ለማምጣት የሚቻለው ደግሞ የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ሲቻል ብቻ መሆኑንም ሸንጎው ለማሳሰብ ይወዳል። እነዚህም፦
  1. ስብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያግዱ አፋኝ ህጎች ሲሰረዙ፥
  2. ሁሉም የኅሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሲፈቱ፥
  3. ፍርድ ቤቶች ከፖለቲካ ቁጥጥር ነፃ ሲሆኑና ፍትህ እንዲሰፍን ሲደረግ፥
  4. ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያሳትፍ በሀገራዊ መግባባት ላይ የተመሠረተ የሽግግር ሂደት እንዲኖር ሲደረግ ነው ።
በህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ የሚካሄደው የርስበርስ  ትርምስ የትኛውም ቡድን አሸናፊ ሆኖ ቢወጣ ከላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች እስካልተሟሉ ድረስ አገሪቷ ላይ የሚደርሰውን የቀውስ አደጋ ሊቀለብስ አይችልም። የኢትዮጵያ ህዝብ  የሚሻው መሠረታዊ ለውጥን ነው። ከዚህ ሌላ ግን የአበው ብሂል እንደሚያሰተምረን “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” ከሚለው የዘለለ ሊሆን አይችልም።
ስለሆነም ወገናችን የናፈቀውን መሠረታዊ ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን ለማድረግ የተቃዋሚ ኃይሎች በጋራ መታገል የግድ ነው።  ከዚህ ሌላ አማራጭ እንደሌለ በመገንዘብ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ትግላችንን በጋራ እንድናካሂድ በተደጋጋሚ ላቀረበው ጥሪ ተቃዋሚ ኃይሎች አወንታዊ ምላሽ እንድትሰጡ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እንወዳልን።
የሕዝብ ድምፅ የማይሰሙ አምባገነኖች መጨረሻቸው ውድቀት ነው!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

No comments:

Post a Comment