Sunday, March 17, 2013

ሰንሰለቱም ይጠብቃል፤ እርግጫውም ይከፋል …ካልተነሳን!




አስተዳደር በየፈርጁና በየደረጃው፤ ከብሄራዊ መንግስት እስከ ታች የቀበሌ አመራር በመጥፎም ይሁን በደግ መልኩ በዜጎች ህይወት የለት ተለት እንቅስቃሴና አኗኗር ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው ሁሉም ሰው እየኖረው ስለሚያየው ማስረጃ መደርደር ላያስፍልገው ይችላል።
በሀገርና በህዝባዊ ጉዳዮች ውሳኔ አሰጣጥ ላይ እናም ውሳኔውን በማስፈጸም ሂደት ላይ ዋናው ተዋናይ በመንግስትነት የተሰየመው አካል ሲሆን፤ እንደየ ሀይላቸውና ቅቡልነታቸው፤ በመንግስት ውሳኔ ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉ ወገኖች መኖራቸው የተለመደ ነው። ለምሳሌ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የሰራተኛ ማህበራት፤ የገበሬ ማህበራት፤ የሙያ ማህበራት፤ ተደማጭ ግለሰቦች እናም አለም አቀፍ ሀይላት፤ የመገናኛ ብዙሀን፤ የገንዘብ ተቋማት፤ ወዘት……ከሁሉም  በላይ ደግሞ ሕዝብ!!..ዲሞክራሲ ባለበት ሀገር ውስጥ በመንግስት ውሳኔ ላይ ተጽእኖ ማሳደር ይችላሉ።
ወደእኛ ሀገር ጉድ የመጣን እንደሆነ በተለይም በደርግና በዘረኛው የወያኔ አስተዳደር ዘመን ፍጹም በሆነ ወደር ያልተገኘለት አንባገነንነት ስር በመውደቃችን፤ የምንታገልለትና የምንመኘው ዲሞክራሲ ጭላንጭሉም እስከወዲያኛው በመጥፋቱ፤ እንኳን የፖለቲካ ድርጅት፤ እንኳን የሙያ ማህበር፤ ህዝብ በነቂስ ከቤቱ ወጥቶ አደባባይ ውሎ አድሮ አቤቱታ፤ሮሮም ሆነ ተቃውሞ ቢያሰማ ወያኔ ከጥፋት አቋሙ ፍንክች እንደማይል ለኢትዮጵያ ህዝብ በተግባር አሳይቷል። ሙስሊም ወንድሞቻችን ከአመት በላይ በሰላም እየታገሉለት ያለው የሀይማኖት ነጻነት ምላሽ ማግኘት ቀርቶ ጭራሽ ይህን አንገብጋቢ ህዝባዊ ሰብአዊ ጥያቄ ወደ ወንጀልነት ቀይሮ፤ ንጹሀን ዜጎችን ወህኒ መቀመቅ ለማጎር ወያኔ የሚያደርገውን ሩጫ እየተመለከትን ነው አዲስ ነገር ባይሆንም።

የሙስሊም ወንድሞቻችን ትግል አርአያነቱ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በእልህና በድንቁርና ለሚታመሰው ለሚተራመሰው አለም በሀገራችን ቢሳካም ባይሳካም እየሞቱ እንዴት ሰላምን ማምጣት እንዴት መብትና ንጻነትን ማስከበር እንደሚቻል የሚያስተምር አጋጣሚ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ይህንን የሙስሊማን ወርቃማ የትግል ስልት ለመቀላቀል የዘገየበት ምክንያቱ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ሰላማዊ ትግል መርጠናል የሚሉን የፖለቲካ ድርጅቶች ደጅም ሆነ እቤት ያሉት፤ ከዚህ የተሻለ ሰላማዊ ትግል ምን አለ ብለው ይሆን የራሳቸው አንሶ ህዝቡንም ይዘው የተኙት? ኢትዮጵያ የሙስሊምና የክርስቲያን ሀገር አይደለችም እንዴ? ፖለቲከኞች እስላም ወይ ክርስቲያን አይደሉም እንዴ?…ጥያቄው እኮ የመብት የነጻነት ነው?….የአምልኮ ነጻነት… የፖለቲካ ነጻነት….የኢኮኖሚ ነጻነት….የመኖር ነጻነት… የመደራጀት…..የመሰብሰብ….ሁሉም ልንታገልላቸው የሚገባ ሊኖሩን የሚገቡ የህይወት እሴቶች፤ እስትንፋሶች ናቸው።
መልካም አስተዳደር የሚባለው የአመራር አይነት ቢያንስ ሊኖሩት የሚገቡ ግብአቶች  በግልጽ ተቀምጠው እያለ፤ የተባብሩት መንግታት ድርጅትም ሆነ የአለም ገንዘብ ድርጅት፤ የአለም ልማት ድርጅቶች፤ ሀያላን መንግስታት እነ አሜሪካም ሆኑ እንግሊዞች በተለይም ከአፍሪካ አገሮች መንግስታት ጋር የሚኖራቸው የእርዳታና የልማት ትብብር የሚወሰነው የመልካም አስተዳደር መስፈርቶችን ማሟላት ሲችሉ ነው ቢሉም የግል ጉዳያቸውንና ጥቅማቸውን እስከጠበቁላቸው ድረስ ከማንኛውም ዘረኛና ጨፍጫፊ ቡድን ጋር እንደሚተባበሩ በተግባር አሳይተውናል።
ለዚህም አንድ ቁልጭ ያለ ማስረጃ አሜሪካ በየአለሙ ያሉ አንባሳደሮቿ በሚስጥር ለመንግስታቸው የሚያስተላልፉትን መረጃ ያዝረከረከው ዊኪሊክ  ይፋ እንዳደረገው፤ አዲስ አበባ ያለው የአሜሪካ ኢንባሲ እለት በእለት ወያኔ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች፤ ሰባዊ መብት ረገጣዎች፤ ግድያዎች፤ በአዲስ አበባ ያካሄዱትን ፍንዳታዎች ሁሉ በየእለቱ ለአሜሪካ መንግስት ያስተላልፍ ነበር። ያ ማለት እለት በእለት የምትሰራዋን ወንጀል በሙሉ ያውቁ ነበር። ያውቃሉም። ነገር ግን ባካባቢው የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ስለሚጠብቅላቸው ብቻ፤ በሀገሩና በህዝቡ ላይ ይህን አደረሰ ብለው፤ ትብብራቸውንና እርዳታቸውን አላቋረጡም። አያቋርጡምም። እንግሊዝ በቅርቡ በብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ በሱማሌ ክልል ሀዝቡን የሚያሰቃዩበት ፖሊስ በብዛት አሰልጥኖላቸዋል።
ለውስጥ ችግራችን መፍትሄ ወደ እነሱ መመልከት ሳይሆን እኛው የጉዳዩ ባለቤቶች የችግሩ ገፈት ጨላጮች፤ በመናበብ፤ በመደማመጥ፤ በመተያየት፤ ከየትኛውም የሀገሪቱ ጥግ የበደል ጩኸት ሲሰማ፤ እንደ ንብ አብሮ መቀስቀስና ባንድ ድምጽ በመጮህ የወያኔን ዘረኛ አጥፊ ቡድን መታገልና ከስልጣን ማስወገድ ያስፈልጋል።
በሀገራቸው ፖለቲካና ኢኮኖሚ እንዲሁም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ዜጎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሙሉ የተሳትፎ መብትና እድል ሲኖራቸው፤ የመደራጀት ነጻነት ያለገደብ፤ ኢንፎርሜሽን የማግኘት ነጻነት ያለገደብ ሲኖራቸው፤ በሚወከሉበት ድርጅትም ሆነ በግላቸው በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ደህንነታቸውን፤ ሀብታቸውን፤ ግዛታቸውን፤ መንግስታቸውን፤ በተመለከተ ሊናገሩ ሊደመጡና ውሳኔም ሊያስተላልፉ ሲችሉ፤ ሊሾሙና ሊሽሩ ሲችሉ፤  ቢያንስ መሰረታዊ መብት አላቸውና ወደው ወይም መርጠው ስለተቀበሉት ስርአት የሚያስጨንቅ ነገር የለም፤ ካልበጃቸው ያንኑ መብታቸውን ተጠቅመው ይለውጡታልና!
አለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ቢያንስ ለግማሽ ምእተ አመት ለዲሞክራሲና ለተሻለ መልካም አስተዳደር ትግል ቢያደርግም ባለፉት ሁለት አጋጣሚዎች ድሉን እየተነጠቀ ለእኩይ አላማና ግብ የተነሱ፤የሀገርና የህዝብ  የውስጥ ጠላቶች አሸናፊ ሆነውበት፤ ለባሰ ውድመትና መከራ ዳርገውት፤ ሀገራዊ ህልውናውንም ማጥፋት በሚያስችል የታሪክ አዘቅት አፋፍ ላይ አቆሙት። ዲሞክራሲው ቀርቶ የአንዲት ኢትዮጵያ ህዝብነታችን፤ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ባለቤትነታችን በቀጭን ክር ላይ የተንጠለጠለ እጣፈንታ ሆኖ አረፈው። ዜጎች ተወልደው ካደጉበት አገር እንደ ባእድ ስደተኛ ሀብትና ንብረታቸውን እየተቀሙ ሲባረሩ፤ በተፈጠሩባት ምድር መድረሻ እንዲያጡ ተደርገው በየጎዳናው ሲወድቁ እያየን ምንም ማድረግ ተስኖን አፍጠን ተቀምጠናል።
በደቡብ ኢትዮጵያ፤ አማራ የተባለ ዜጋ፤ በሶማሌ ክልል  ጂጂጋ ሱማሌ ያልሆነ ሁሉ ንብረቱ እየተቀማ፤ እየታሰረ ቶርች እየተደረገ፤ እዚያው ተወልደው ያደጉ አማሮችና ሌሎች ብሄረሰቦች ግፍ እየተፈጸመባቸው ይህንን ተከታታና የማይቆም በእቅድ የተያዘ ጥቃት ማስቆም የቻለ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ድርጅት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ብቅ ባለማለቱ የኢትዮጵያውያኑ ሰቆቃ እየባሰ በመሄድ ላይ ይገኛል። ወያኔና የክልሉ የወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚ  የሱማሌ ባለስልጣናትና ፖሊሶች በመተባበር ይህን ዘመቻ ሲያንቀሳቅሱ፤ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ አለም አቀፍ ሰብአዊ ድርጅቶች ድርጊቱን ለማስቆም ያንቀሳቀሱት ሁለገብ ዘመቻ የለም። የህውሀትና የክልሉ ቅጥረኞቻቸው ዘመቻ ግን አላቋረጠም። ባጠቃላይ ወያኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን ህዝብና ኢትዮጵያን የማጥፋት ቀጣይ ተግባሩን ያለምንም እንቅፋት ማከናወኑን ቀጥሏል።  እራሳችንንና ሀገራችንን ለማዳን መነሳት ያስፈራን በሚምስል መልኩ የወያኔ መንጋ መጨፈሪያ መሆናችን ቀጥሏል።
ያለ ህዝብ ምክርና ዝክር መላውን የሀገራችንን መሬት ለባእዳን አሳልፎ መስጠቱ ቀጥሏል። ነገ ልጆቻችንን በገዛ ምድራቸው ላይ እያሳደዱ እሚገሏቸው ባእዳንን በብዛት እያስገቡ ማስፈሩ ቀጥሏል። በፍርሀት ተውጠን፤ ሀሞታችን ሸንቶ፤ እኛ አባቶቻቸው፤ ወንድሞቻቸው ተቀምጠን የልጆቻችንን ቅርስ ምድር ኢትዮጵያን ወያኔ ሲቸበችበው ዝም ብለናል።
ጀግና ህዝብ ታግሎ ዜጎች ነጻ ዳኝነት የሚያገኙበት ሉአላዊ የሆነ የፍትህ ተቋም ይገነባል። ዜጎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል የሚዳኙበት፤ መብታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ ከሙስናና ከወገንተኝነት በጸዳ የፖሊስ ሰራዊት የአካልና የህግ ጥበቃ የሚያገኙበት፤  ስርአት ይገነባል። ዳኞች ከሙስናና ከአንድ ወገን ጉዳይ አስፈጻሚነት በጸዳ ህሊና ለዜጎች ደህንነት የቆሙ  መሆኑን ያለ ማንም ባለስልጣን ጣልቃ ገብነት በሚሰጡት  ነጻ ፍትህ ያረጋግጣሉ። ይህ በትግላችን እውን ሊሆን የሚገባው ስርአት ሀገራችንን እንደሰማይ እየራቃት፤ በመሄድ ላይ ይገኛል። በራሳችን ደካማነትና ፍርሀት።
በሀገርና በህዝብ ጉዳይ ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎች፤ የሚተገበሩ እርምጃዎች፤ ህግና ደንብን የተከተሉ መሆናቸውን እርግጠኛ ለማድረግ፤ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ህዝብ እያያቸው፤ እየሰማቸው፤ እየተነገረው፤ እየተነጋገረባቸው ሲሆን ፍትሀዊነት ይሆናል። በመንግሰትነት የተሰየመው አካል ያስተላለፈው፤ የሚያስተላልፈው ውሳኔ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነካው የህብረተሰብ አካል፤ ቀጥተኛ ኢንፎርሜሽን ቀድሞ ሲያገኝና የሀሳቡ ተካፋይ ሲሆን፤ ጥቅሙንም ደህንነቱንም ለመጠበቅ እድል ያገኛል። በህብረተሰብ ህይወት ላይ የሚተላለፍ ውሳኔ ሰፊና ጥልቅ ምክክር ያስፈልገዋል።
ልንታገሰው የሚገባ መንግስት፤ አስተዳደር፤ ከህዝብ ለሚመጡ ሮሮዎችና አቤቱታዎች የመብት ረገጣ፤ የፍትህ ጉድለት፤ የመሳሰሉ ችግሮችን ፈጥኖ መስማትና መፍትሄ ለመሻት መንቀሳቀስ የሚችል መሆን ይጠበቅበታል። በንቅዘት የበሸቀጡ ባለስልጣናት ከደሞዛቸው ጋር የማይመጣጠን ኑሮና ንብረት ሲያደረጁ ያየ ህዝብ፤ የሀገር ሀብት ለግል ጥቅም እየዋለ ነው ብሎ ቢያመለክት፤ መንግስት ውሎ ሳያድር እነዚያን ግለሰቦች የሀብታቸው ምንጭ ምን እንደሆነ እንዲያስረዱ ለዳኝነት የሚቆሙበትን የህግ ተቋም ማደራጀትና ጉዳያቸው ታይቶ ለጠያቂው ህዝብ ምላሽ የሚሰጥበትን ሂደት እውን ያደርጋል። ሌባውና ወንጀለኛው፤ ሙሰኛው እራሱ መንግስት ነኝ ብሎ ስልጣን ላይ የተጣበቀው ወገን በሆነበት ሀገር ከላይ የጠቀስኩት ነገር የማይታሰብ ነው። ብቸኛው አማራጭ አንባገነኑን ቡድን ከስልጣን አስወግዶ፤ በከርሰ መቃብሩ ላይ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት ነው።
ቀጣይነት ላለው የህብረተሰብ እድገትና ሰላም አስፈላጊ የሚሆነው፤ የህዝብን ታሪክ፤ ባህል፤ ማህበራዊ አኗኗርና መስተጋብር፤ የለት ተለት ያኗኗር ዘይቤን ግንዛቤ ውስጥ የሚያካትት ውሳኔና እርምጃ የሚያራምድ አስተዳደር መኖር ነው።

በህብረተሰብ ውስጥ እጅግ የተለያዩና አንዳንዴም የተራራቁ ፍላጎቶች አመለካከቶች መኖራቸው የተፈጥሮ ህግ ነው። እያንዳንዱን የህብረተስብ ክፍል እኩል ማስደሰት አይቻል ይሆናል። እስላምና ክርስቲያን በጋራ በሚኖሩባት ሀገር ውስጥ የክርስትያኑን ህዝብ ፍላጎትና መብት ከግምት ውስጥ ባለማስገባት አንድ ገዢ ቡድን ተነስቶ በሸሪአ ህግ ነው መተዳደር ያለብን በሚል፤ የእስላም መንግስት ቢያውጅ፤ በአንዲት የጋራ ሀገር ውስጥ ያንዱ ወገን ፍላጎትና ጥቅም የሌላውን ወገን ጉዳትና ቅሬታ አስከተለ ማለት ነው ። ለእንዲህ ያለ ህዝብ ሁሉንም የሚያስማማው አለማዊ መንግስት ይሆንና ሁሉም የማምለክ ነጻነቱ ተከብሮለት ሲኖር ማለፊያ አሰራር ይሆናል።
የህብረተሰብ ደህንነት የሚረጋገጠው፤ እያንዳንዱ ክፍል ከህዳጣን እስከ ብዙሀን ሕዝቡን የገነቡ ብሄረሰቦች  እኩል መብትና ነጻነት ሲኖራቸው፤ በሀገራቸው እኩል የባለቤትነት ስሜት ሲኖራቸው፤ በባህላቸው፤ በቋንቋቸው፤ በሀይማኖታቸውና በኑሮ ደረጃቸው ምክንያት ያለመገፋት፤ ያለመገለል፤ መኖሩን በተጨባጭ ማየት ሲችሉ ነው።
በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ቀና ብሎ እንደልቡ እየተናገረ መኖር የያዘ ዜጋ ወያኔ ብቻ ሆኗል። ሰፊው ህዝብ ተሸማቆ በመኖር ላይ ነው። በግል መኖሪያ ቤቱ ውስጥ እንኳ እንደፈለገ የፈለገውን ጮክ ብሎ ማውራት እያስፈራው መቷል። የወያኔ ጆሮ ጠቢዎች በየሰዉ ጣራ ስር ጨለማ ለብሰው እየተለጠፉ ዜጎች የሚያወሩትን ወሬ እየሰበሰቡ ለቅርብ ሀላፊያቸው ያቀርባሉ። ፈጥኖ ፈጥኖ ከውጭ አገር ስልክ የሚደወልላቸው ሰዎች ይተኮርባቸዋል። አንዳንዶች በቤታቸው ዙሪያ ማንም እንዳይቆም ስልክ ሲደወልላቸው ልጆቻቸውን አሰማርተው ነው እንደልብ የሚያወሩት።
ተጠያቂነት የጤናማ መንግስት ያስተዳደር ስራ ደንብ ነው። የመንግስት ተቋማትና  ባለስልጣናት ብቻም አይደሉም፡ የግል ድርጅቶች ማህበራትና ተቋማት ጭምር የሀይማኖት የእምነት እና የሙያ ማህበራት ጭምር ሀላፊነት ለጣለባቸው ወገን፤ ለሚያገለግሉት ህዝብና ለሚተዳደሩበት ህግ ተጠያቂ ናቸው። ተጠያቂነት ግልጽነትንና ለህግ ተገዥነትን ያካትታል። ተጠያቂነት የዲሞክራሲ ስርአት አንኳር ግብአት ነው። የመንግስት ባለስልጣናትና ሀላፊዎች እንደየደረጃቸው በህግ የሚሰጣቸው ስልጣንና ሀላፊነት አለ። ያ ህጋዊ ስልጣንና ሀላፊነት ለሚያስተዳድሩት ህዝብ አገልግሎት የሚሰጡበት ልክና ደረጃ ነው። ተጠያቂነቱ ስልጣናቸውን ባግባቡ እየተጠቀሙ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስገድዳቸው ያሰራር ፈርጅ ነው።
አሁን በሀገራችን ጥያቄው ተጠያቂነት አለ ወይስ የለም አይደለም። በሀገራችን ተጠያቂነት የለም። ስርአቱን ሙሉ ለሙሉ እከምናስወግድ ድረስ እንኳን ቢሆን እስካሁን ለፈጸማቸው ወንጀሎች ይህን ገዢ ቡድን እና ባለ ስልጣናቱን እንዴት ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል? ተቆጥሮ ከማያልቀው ወንጀላቸው የቅርቡን “ጂሀዳዊ ሀረካት” እንውሰድና የዜጎችን መብትና ነጻነት፤ ሰብአዊ መብት በእጅጉ የረገጠ፤ ለይስሙላ አለ የተባለውን ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር፤ በፍርድ ሂደት ላይ ያለን ጉዳይ በመገናኛ ብዙሀን በማሰራጨት ተራ የፖለቲካ ጠቀሜታ ለማግኘት መንግስት ነኝ ያለ ቡድን  የፈጸመው ወንጀል ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ማስታወቂያ ሚኒስትሩን በተዋረድ የተሳተፉትን በሙሉ ለፍርድ ማቅረብ ያስፈልጋል። ይህ ፊልም የታለመለት ወንጀል የሙስሊም ወንድሞቻችንን ሰብአዊ መብትና  የሀይማኖት ነጻነት መጋፋት ብቻ ሳይሆን ህዝብን ከህዝብ፤ ክርስትያንን ከሙስሊም ለማጋጨት ሆን ብሎ ይህ ስልጣን ላይ ያለው ማፊያ ቡድን ያዘጋጀው ወንጀል ነው። የህውሀት ምግብ ለስራ ሰራተኞች የተሰበሰቡበት ምክር ቤት፤ ስልጣኑ የሚፈቅድለትን ነገር ባለማድረጉ፤ የዚህን ወንጀል ፈጻሚዎች ለጥያቄ ባለማቅረቡ ለራሱም መጠየቅ የሚገባው፤ መበተን የሚገባው የመንጋ ጥርቅም ነው።
የወያኔው ተረት ተረት ህገመንግስት አንቀጽ 12 ንኡስ አንቀጽ 2 ማንኛውም ሀላፊና የህዝብ ተመራጭ ሀላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል ይላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪዎች ናቸው። ሚኒስትሮችም በውሳኔአቸው ተጠሪዎችና ተጠያቂዎችም ናቸው። በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ወንጀል ይፈጸማል። ጠያቂም ተጠያቂም የለም። ወያኔን ከስልጣን በማስወገድ ለፈጸሙት ወንጀል ሁሉ ሁሉንም ለፍርድ በማቆም ተጠያቂነትን ማስተማር ይገባናል። ፖሊስ የህሊና እስረኞችን ቶርች በማድረግ፤ ያልፈጸሙትን ወንጀል እንደፈጸሙ አድርጎ በስቃይ እንዲናገሩ በማድረግና ያንን በቴፕ በመቅዳት፤ ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ፤ ህዝብ በመገናኛ ብዙሀን እንዲሰማውና መቀጣጫ አድርጎት አርፎ እንዲቀመጥ ለማድረግ፤ ወደር የማይገኝለት ግፍ በንጹሀን ዜጎች ላይ በመፈጸሙ፤ የደህንነቱ ክፍል የዜጎችን የግል ሚስጢር ለመሰብሰብ፤ የስልክ፤ የኢሜል፤ የፖስታ መልክቶችን በመጥለፍ፤ በመስረቅ፤ በከፍተኛ ወጭ አንድ ሰላይ ለአምስት ዜጋ በመመደብ ህዝቡ የህሊና ሰላም አቶ እንዲኖር፤ በጭንቀት ተወጥሮ ስለግሉ ደህንነት እየሰጋ በወያኔ ገዢ ቡድን ላይ እንዳይነሳ ለራሱ ተሸብሮ እንዲኖ ሴራ በመኖንጎን፤ ዳኞች ህሊናቸውን ለጥቅም በመሸጥ የሀሰት ምስክርና የውሸት ክስ፤ የሀሰት ማስረጃ ተቀነባብሮ ሲመጣላቸው ህሊናቸው እያወቀ፤ የአረመኔዎቹ መንግስት ጠባቂና ተንከባካቢ በመሆን ንጹሀን ዜጎችን በሞትና በእድሜልክ እስራት ፍርድ በመቅጣታቸው፤ ሁሉም የጃቸውን ማግኘት ይገባቸዋል። ለፍርድ መቅረብ ይገባቸዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህን በጉልበት ስልጣን ላይ ተጣበቀው፤ እየገደሉ፤ እያፈኑ፤ ወህኒ እያጎሩ፤ እያሸበሩ ስልጣን ላይ ለመዝለቅ የቆረጡ የህውሀት  አመጸኞችን በአመጽ አስወግዶ፤ እውነተኛው ፍትህ ርትእ የሚነግስበትን ስርአት ገንብቶ፤ ዛሬ ግፍ እየፈጸሙበት ያሉትን ወያኔና ቅጥረኞቻቸውን ሁሉ እግር ተወርች አስሮ ለዳኝነት ማቆም ያስፈልጋል።
የጊዜ ጉዳይ ነው። እድሜልኩን ተኝቶ ሲረገጥ የኖረ ህዝብ በአለም ላይ የለም።  የኢትዮጵያ ህዝብም ተረግጦ ለመኖር አይደለም የተፈጠረው:: ታፍኖ፤ ተረግጦ፤ ተገድሎ በዚህች በሰለጠነች አለም ውስጥ ለምእተ አመት ያህል በመኖር ሁሉንም መከራ አጣጥሞታል። ብዙ የግፍ ጽዋ ተጎንጭቷል፤ እየተጎነጨም ነው። አሁን የቀረው ነገር ማንንም ሳይጠብቅ አንድ ቀን መገንፈል። የቀረው ነገር…. በቃ! ብሎ በአንድ ድምጽ፤ አንድ ቀን መፈንዳትና እነኚህን የወረሩትን ትንኞች ከትከሻው ላይ ማርገፍ…. ማውረድ ብቻ ነው!
ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!…ሞት ለዘረኞች

No comments:

Post a Comment