Wednesday, March 20, 2013

ያ ትውልድ ይመስክር



                                                       
                                                           እራሱን ቢያመጣ ታሪክ ተመልሶ

                                                           ዛሬም አለሁ ቢለን የትናንቱን ጥሶ

                                                           ያሳየን ይሆን ወይ የዚያን ዘመን ትውልድ

                                                            እንደ ሻማ ቀልጦ ለሌላው የሚነድ

                                                                 
                                                                    ያ ትውልድ ! ለጠላት ዓላማ ያላጎበደደ

                                                                   ታሪክን ያልናደ እውነትን ያልካደ

                                                                   ግንባሩን ሳያጥፍ ከጠላት ተናንቆ

                                                                    ስንቱን አፈር በላው ስንቱ ቀረ ወድቆ ፤

                                                                     በደሙ ጠብታ በአጥንቱ ክስካሽ

                                                                     ተጠየቅ ለሚሉት እየሰጠ ምላሽ

                                                                      አለፈ ያ ትውልድ ላናየው ዳግመኛ

                                                                      ያደራ ቃል ትቶ፡ አስረክቦ ለኛ ፤

ቋንቋ የሕወሃት የጥፋት ሚዛን እና የመጭው ዘመን የኢትዮጵያዊያን ስጋት



ልቃቂት ነው ሂዎት፤ በእንዝርት ላይ እንደሚሽከረከረው የጥጥ ንድፍ ዘለላ እየተጠማዘዘ እየተሽመለመለ፣ እየጠበቀና እየላላ፣ እየተወጠረና እየረገበ የሚጠመጠም የሂዎት አንጓ። ያንዱ ሂዎት ዘርፍ በሌላው መሰረት ላይ እየተመጠነና እየተደረበ የሚከወን ኩነት። የስረኛው የላይኛውን ተሸክሞ፣ የላይኛውም በስረኛው ላይ ያለጭንቀት ተመቻችቶና ተንደላቆ የሚቀመጥበት ልቃቂት ነው ሂዎት። ደግሞም እንደ ታሪክ የሚመዘዝ፣ የሚተረክ እንደ ልቃቂት የፈትሉን ጫፍ ይዘው የሚተረትሩት የሚያወጉት፤ ክፉ ደጉን፣ ሳቅ ዋይታውን፣ የጀግንነት የፍቅር ወጉን፣ ያንን ዘመን ያን የጥንቱን፣ የነንቶኔን የነንቶኔን፣ ምርቃቱን ቱፍቱፍታውን፣ የልጅነት ያፍላነቱን፣ የሚያሳየን የሚያሞቀን፣ ወዲያው ደግሞ የሚያበርደን፣ አበሳጭቶ የሚያነደን፣ አስደስቶ የሚያነጥረን፣ ያው ሂዎት ነው ልቃቂቱ፣ የጥንት ያሁን ወደፊቱ፣ እናም እንዲህ እንዲህ ብሎ፣ ስቃያችን አበሳችን ፉከራችን በያይነቱ ተጠቅልሎ፣ አሁን እኛ ከለንበት እኔ ዛሬ ከማወራው፣ ታሪክ አንጓ እንኳ ለመድረስ 68 ዓመት ሞላው። ይችን ትንሽ የታሪክ ጫፍ፣ ይዘን ሽምጥ ስንከንፍ፣ ልክ ከ68 ዓመት ደጃፍ፣ ሆሎኮስት ነው የሚገዝፍ። ከምስራቅ ጫፍ ጃፓን ጠረፍ፣ እስከ አሜሪካ ዳር ድንበር ጽንፍ፣ ከሩሲያ ጀርመን ጓዳ፣ ሳውዝ አፍሪካ ድረስ የፈነዳ፣ የዓለምን ቅስም የሰበረ፣ ያማረረ ያሳረረ፣ አውራ ኩነት እኩይ ተግባር ይህ ነበረ። እኔም እንግዲህ ዛሬ፣ ከታሪክ አንጓ ቆንጥሬ፣ ከሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር እየቃኘሁ፣ ዝግጅቴን ያው ለእናንተ ብያለሁ።
ኩነቱ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በቅርብ ርቀት የተከወነ ቢሆንም ለወቅቱ ከፍተኛ የሚባል ዝግጅት ተደርጎበታል። ዓለምን በሁለት ጎራ አቧድኖ አቆራቁሷል አፋጅቷልም። እስከ አሁንም ድረስ ለማሰብ የሚያዳግቱ፣ ለማስታወስ የሚዘገንኑ፣ ለማየት የሚቀፉ በፍርሃት የሚያርዱ ድርጊቶች ተከውኖበታል። በወቅቱ የወደመውን ንብረት የጠፋውን ሃብት መጠን ለጊዜው እንተወውና ስድስት ሚሊዮን አውሮፓዊያን ይሁዲዎችን ጨምሮ ካስራ አንድ ሚሊዮን በላይ ንጹሃን ዜጎች ሂዎታቸውን ገብረውበታል- ሆሎኮስት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት።

የኢህአዴግ አፋኝ አስተዳደር የአፓርታይድ ቅርጽ እየያዘ ነው!



ሰማያዊ ፓርቲ
ዛሬ መጋቢት ስምንት ቀን 2005 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት ማህበር፤ ሰማያዊ ፓርቲ እና ባለራዕ ወጣቶች ማህበር በጋራ በመሆን “ለፋሽስቱ የጦር ወንጀለኛ ለማርሻል ግራዚያኒ ክብር መስጠት የአባቶቻችን መስዋዕትነት ማራከስ ነው” በሚል የተጠራውን ሰልፍ አምባገኑ የኢህአዴግ መንግስት በርካታ የፌደራል ፖሊስ፣ የደህንነት አባላትን እና የአዲስ አበባ ፖሊሶችን በማሰማራት ሲበትን፤ የተቋማቱን ከፍተኛ አመራሮች፤ ታዋቂ ግለሰቦች እና በርካታ ወጣቶች ጨምሮ ቢያንስ 34 ሰዎች አስሯል የታሳሪዎች ቁጥር አሁንም በመጨመር ላይ ነው፡፡የኢህአዴግ አፋኝ አስተዳደር የአፓርታይድ ቅርጽ እየያዘ ነው!
እንዲሁም በትላንትናው እለት ለተቃውሞ ሰልፉ የቅስቀሳ ስራ ሲሰሩ ከነበሩት ውስጥ 2 የሰማያዊ ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ አባላትን እንዲሁም የባለራዕይ ወጣቶች የስራ አስፈጻሚ አባላትን ጨምሮ 8 ሰዎችን አስረዋል፡፡
በአሁኑ ሰአት በእስር ላይ የሚገኙት እና ስማቸው የተገኘ
1. ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም
2. አቶ ታዲዎስ ታንቱ
3. አቶ ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ሊቀመንበር)
4. ስለሺ ፈይሳ (የሰማያዊ ም/ሊቀመንበር)
5. ይድነቃቸው ከበደ (የሰማያዊ የህግ ጉዳይ ሀላፊ)
6. ሀና ዋለልኝ (የሰማያዊ የሴቶች ጉዳይ ሀላፊ)
7. ጌታነህ ባልቻ (የሰማያዊ የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ)
8. ብርሀኑ ተክለያሬድ (የባለራዕይ ወጣቶች ተ/ምክትል ሊቀመንበር)
9. ያሬድ አማረ (የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ጸሀፊ)
10. ኤልሳቤጥ ወሰኔ

Sunday, March 17, 2013

ሰንሰለቱም ይጠብቃል፤ እርግጫውም ይከፋል …ካልተነሳን!




አስተዳደር በየፈርጁና በየደረጃው፤ ከብሄራዊ መንግስት እስከ ታች የቀበሌ አመራር በመጥፎም ይሁን በደግ መልኩ በዜጎች ህይወት የለት ተለት እንቅስቃሴና አኗኗር ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው ሁሉም ሰው እየኖረው ስለሚያየው ማስረጃ መደርደር ላያስፍልገው ይችላል።
በሀገርና በህዝባዊ ጉዳዮች ውሳኔ አሰጣጥ ላይ እናም ውሳኔውን በማስፈጸም ሂደት ላይ ዋናው ተዋናይ በመንግስትነት የተሰየመው አካል ሲሆን፤ እንደየ ሀይላቸውና ቅቡልነታቸው፤ በመንግስት ውሳኔ ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉ ወገኖች መኖራቸው የተለመደ ነው። ለምሳሌ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የሰራተኛ ማህበራት፤ የገበሬ ማህበራት፤ የሙያ ማህበራት፤ ተደማጭ ግለሰቦች እናም አለም አቀፍ ሀይላት፤ የመገናኛ ብዙሀን፤ የገንዘብ ተቋማት፤ ወዘት……ከሁሉም  በላይ ደግሞ ሕዝብ!!..ዲሞክራሲ ባለበት ሀገር ውስጥ በመንግስት ውሳኔ ላይ ተጽእኖ ማሳደር ይችላሉ።
ወደእኛ ሀገር ጉድ የመጣን እንደሆነ በተለይም በደርግና በዘረኛው የወያኔ አስተዳደር ዘመን ፍጹም በሆነ ወደር ያልተገኘለት አንባገነንነት ስር በመውደቃችን፤ የምንታገልለትና የምንመኘው ዲሞክራሲ ጭላንጭሉም እስከወዲያኛው በመጥፋቱ፤ እንኳን የፖለቲካ ድርጅት፤ እንኳን የሙያ ማህበር፤ ህዝብ በነቂስ ከቤቱ ወጥቶ አደባባይ ውሎ አድሮ አቤቱታ፤ሮሮም ሆነ ተቃውሞ ቢያሰማ ወያኔ ከጥፋት አቋሙ ፍንክች እንደማይል ለኢትዮጵያ ህዝብ በተግባር አሳይቷል። ሙስሊም ወንድሞቻችን ከአመት በላይ በሰላም እየታገሉለት ያለው የሀይማኖት ነጻነት ምላሽ ማግኘት ቀርቶ ጭራሽ ይህን አንገብጋቢ ህዝባዊ ሰብአዊ ጥያቄ ወደ ወንጀልነት ቀይሮ፤ ንጹሀን ዜጎችን ወህኒ መቀመቅ ለማጎር ወያኔ የሚያደርገውን ሩጫ እየተመለከትን ነው አዲስ ነገር ባይሆንም።

Tuesday, March 12, 2013

እኛና እነሱ – የሁለት ሀገር ሰዎች ነን


እም! ብዬ እያማጥኩ ጀመርኩት።
eprdf leanders in ethiopia
(ፎቶ – ከኢትዮጵያ ከረንት አፊርስ ዲስከሽን ፎረም የተወሰደ)
እኛ ማነን? እኛ የተቀመምንበት ኢትዮጵያዊነት የሚያንገበግበን። ችግሯ – ችግራችን፤ ዕንባዋ – ዕንባችን፤ መከፈቷ – መከፈታችን፤ ጉስቁልናዋ – ጉስቁልናችን፤ አንገት መድፋቷ ሃዘናችን የሆነው በዬትኛውም ዓለም የምንገኝ ልጆቿ ነን። በወያኔ መዳፍ ውስጥ አሳሩን በማዬት የሚገኘው ከስሜን እስከ ደቡብ ጫፍ፤ – ከዱቡብ ጫፍ እስከ ምዕራብ ጫፍ፤ ከምዕራብ ጫፍ እስከ ምስራቅ ጫፍ የሚገኝ ህዝብ ለሀገሩ ልዩ መለዮችን የሆነው ሥጋና ደም ነን።
እነሱስ? „የደላው ገንፎ ያላምጣል“ እንዲሉ ከማህደረ – ኢትዮጵያዊነት ትንሽ ልቅላቂ ያልፈጠረላቸው፤ አለቶች … በዕንባ ላይ ይሾማሉ፤ ይሸለማሉ …. ልጆቻቸውን አንደላቅው ያሰተምራሉ፤ ሲሰኛቸው ውጬ ልከው ዶላር አፍሰው ያዝመነምናሉ።
ባይታዋሩ ወገናችን ደግሞ ዕጣ ፈንታው … ሥራ ፍለጋ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን፤ በውሃ ጥም፤ በመንገድ ጉዞ አቅም በማነስ፤ በውሃ ሙላት፤ በጾታ ጥቃት፤ በቀጣሪ ዳባ እንደተበተነ ያልቃል፤ እንዲሁም ካሰቡት ሳይደርሱ የአሞራ እራት ይሆናል። በስደቱ በእሳት የሚቀቀሉት፤ ከፎቅ ተከስከስሰው የሚሞቱት፤ በጭንቀት በሽታ አብደው አድራሻቸው ጠፍቶ የሚቀሩትንማ ስሌትም አይገታውም። እንደ ጣሊያን በመሳሰሉት ሀገሮችም መንገድ ላይ ተዳዳሪ ወገኖቻችን በሚመለከት — ቤቱ ይቁጠረው።

ለኢትዮጵያ እንድረስላት ይህን ሳናደርግ የቀረን እንደሆነ ግን ህሊና ቢስ ነን ፍሬ ቢስ ነን ወይም ደግሞ ከሃዲ ነን



በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁናቴ ህዝቡ ዕድሉን አግኝቶ ወደውጭ የወጣ እንደሆነ ወደ ዓገር ቤት ተመልሶ ቢገባ የጭንቅላት በሽተኛ ወይም እንደ እብድ አልያም እንደ ሞተ
autor yared elias Brehane

ሰው ተቆጥሮ የህድር ጡሩንባ ተለፍፎ ዘመድ አዝማድ ተሰባስቦ የሚላቀስበት አልያም ደግሞ ከቤተሰብ ትዳር አንስቶ የሰፈር ሰው ትንሽ ትልቁ የስራ ባልደረባ ከታክሲ ሹፌር እስከ ዶክተር እስከ ትልቁ የወያኔ አገዛዝ ሚኒስቴር ድረስ እንደዘመኑ በሽታ ታይቶ የምትገለልበት ወሬው ሁሉ እንትና ደቡብ አፍሪካ ጠፋ በሞያሌ በሱዳን ሊቢያ  እየተባለ ስንቱ  ተስፋ ቆርጦ የሱሰኛ ተገዢ የሚደረግበትዘመን። ሌላው ይቅርና  እትብቱ ወደተቀበረበት ሃገር ለመመለስ እንኳን የወያኔ ገዢ ፓርቲ 10 ግዜ እንድናስብ የሚነግረን ወቅት  እንደነገሩ ተበልቶ አንዲት ለስላሳ ለመጠጣት 20 ግዜ የሚታሰብበት ቢራ ለመጠጣት ዱቤ ለመጠየቅ 40 ግዜ የሚታሰብበት ሃገር።  ስለ እውነት ስለነጻነት ቢጠየቅ ደግሞ ምን ሊሆን እንደሚችል መልሱን ? ..ለነሱ………የሚባለበት ግዜ ።
መቼስ አገሩ ላይ መኖር የሚጠላ ስው ያለ አይመስለኝም ግና ገና አካሉ አገሩ ላይ ቍጭ ብሎ መንፈሱ ውጭ አገር ያለውን ስንቱ ይቍጠረው። በውጭ ሃገር የሚኖረውማ  ወደ ሃገሩ ተመልሶ ሃገሩ ላይ ሃገሩን ወገኑን ለማገልገል የፈለገ ሰው ሃገሪቷ ላይ መኖር የማይችልበትን የጥቂት ዘረኛ ወያኔ አገዛዝ መንግስት የሚኖርባት በመሆኑ ለማድረግ አይችልም። በዛ ላይ ሰሞኑን ያየሁት የሰለሞን ቦጋለ እና ሳምሶን ቤቢ ፊልም በጣም ሲከነክነኝ ነው የዋለው አዎ የዚህ ደራሲ በፈለገው መልኩ ይጻፈው እኔ በተረዳውት ግን ለዚያች አገር ለዛ ህብረተሰብ ነጻነት ያስፈልገዋል ። መልዕክቱን በፈለጉት መልኩ ያስተላልፉት ግን በደንብ የሚታይ ነገር ነበረበት ስለነጻነት ብሩህ ተስፋ ።

Saturday, March 9, 2013

የህወሓት ስረወመንግስት በኢሕኣዴግ ጡዘት


“የህወሃት የበላይነት በእኩልነት”

ተጠፍጥፈው በወያኔ የተሰሩት የኢሕኣዴግ አባል ድርጅቶት እስከዛሬ እንዳልተዋሃዱ የሚታወቅ ነው:: እንዚህ ድርጅቶች ባለፉት 20 አመታት ውስጥ ያልተዋሃዱበት እና በአንድtplf rotten appleፓርቲ እና ግለሰብ ስር እየተሽከረከሩ የኖሩበት ሁኔታ በበረሃው የመሃላ ፖለቲካ አለምብሰላቸው ወደ ሕወሓት ስረወመንግስት ውሳኔ ሰጪነት ሳያሸጋግራቸው የፖለቲካ ባሮች እንደሆኑ አሉ::ርእዮት አለሙ እጅግ ወደ ኋላ የቀረ እና የአስተሳሰብ ጥልቀቶች አለመኖር ፓርታዊ ዲሞክራሲን ማእከል አለማድረጋቸው የውህደት ምህዳሩ እንዲደፈን እና ብሔር ተኮር የውህደት አደረጃጀት ወደ ሃገራዊ ፓርቲነት እንዳይለወጡ ለውህደቱ ዚግዛግ እደምታ አስከትሎበታል::ይህ ደሞ ሕወሓት የበላይነቱን እዳያጣ እና ስረወመንግስት እንዳይደረመስ ከመፍራት በመጣ የተቀነባበረ የፖለቲካ ሴራ ነው::
በባህር ዳር ይካሄዳል ተብሎ እየተጠበቀ ያለው የኢሕኣዴግ ጉባኤ እጅግ በተጠንቀቅ እየተጠበቀ ሲሆን ፓርቲዎች ላለፉት አመታት እየተደረገባቸው ያለውን የፖለቲካ ጭቆና በተመለከተ ያፈነዱታል ተብሎ ተሰግቷል:: ለዚህን በአሁን ሰአት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል:: የግንባሩ አባል ድርጅቶች በሕወሃት ላይ ያላቸውን ጥላቻ ያንጸባርቁበታል ድርጅታዊ መብታቸን በፋት ይጠይቁበታል የተባለለት ይህ ጉባየ ሌሎች ችግሮችንም እንደሚወልድ እየተነገረለት ነው::እነዚሁ አባል ድርጅቶች “የህወሃት የበላይነት በእኩልነት” የሚል አዲስ አስተሳሰባቸውን ይዘው ስለሚቀላቀሉ ፍራቻውን ለማስወገድ ተሳታፊ አባላት ሲመረጡ ጥንቃቄ እንዲወሰድ ስራዎች ተሰርተዋል::በግንባሩ ላይ የለውጥ ተጸኖ ያሳድራሉ የተባሉ ተሳታፊዎች ወደ ባህር ዳር እንዳይዘልቁ በመደረጉ ችግሮች እንዳመረቀዙ ነው ያሉት::

Friday, March 8, 2013

የአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮች ከቤንሻንጉል ክልል እንዲወጡ



ኢሳት ዜና:-በደቡብ ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ የታየው የአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮችን የማፈናቀሉ እንቅስቃሴ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ በመተከል ዞን በቡለን ወረዳ በመደገሙ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ አርሶ አደሮች ክልሉን እየለቀቁ እየወጡ ነው። የአይን እማኞች ለኢሳት እንደገለጡት በአሁኑ ሰአት ልጆቻቸውን ይዘው ፣ የቤት እንስሶቻቸውን እየነዱ መንገድ ወደ መራቸው በመጓዝ ላይ የሚገኙት የአማራ ተወላጆች ከ5 ሺ በላይ ናቸው።
ከ500 ያላነሱ አርሶ አደሮች  የአማራ ክልል ዋና ከተማ ወደ ሆነቸው ባህርዳር የደረሱ ቢሆንም፣ አቤቱታቸውን የሚቀበላቸው ሰው በማጣታቸው ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውን ትናንት ባህርዳር የገቡ ተፈናቃዮች ለኢሳት ገልጠዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን ባለስልጣናት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጉርዳፈርዳ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን በተመለከተ ለፓርላማ ሲናገሩ፣ ተፈናቃዮቹ በህገወጥ መንገድ በመሄድ በክልሉ የሰፈሩ ናቸው በማለት መናገራቸው ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም ከደቡብ ክልል የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች የት እንደደረሱ በውል አይታወቅም። የተለያዩ የተቃዋሚ ድርጅቶች የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት በአማራ ተወላጆች ላይ የሚወስደው እርምጃ ከዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር እንደሚያያዝ ሲገልጹ ቆይተዋል።

ሊበሉ ያሰቡትን አሞራ ይሉታል ጅግራ!

ሊበሉ ያሰቡትን አሞራ ይሉታል ጅግራ!

Thursday, March 7, 2013

የህወሓት/ኢህአዴግ የውስጥ ፍጥጫ፣ ዴሞክራሲን አይወልድም


የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) በአገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ ያለው አምባገነን አገዛዝ ሕዝባችንን ከዕለት ወደ ዕለት  ለከፋ ስቃይ እየዳረገው እንደሆነ በተደጋጋሚ አስገንዝቧል።  አሁን ደግሞ አምባገነኑ አገዛዝ እራሱ ሊወጣ ወደማይችልበት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እየተዘፈቀ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል።የመለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ በህወሓት/ ኢህአዴግ ውስጥ የሚታየው ግልፅ ሽኩቻና  ፍትጊያ እጅግ እየተፋጠነ መሄዱ ይህንኑ ሃቅ ያረጋግጣል።
ይህንን  ፉክክር የሚያካሂዱት የድርጂቱ አባላት በተወሰነ ደረጃ ይቀያየሩ እንጂ፣ በመሠረታዊነት ቢያንስ ሁለት ቦታ ተፋጠው የሚገኙ ቡድኖች መከሰታቸውን መገንዘብ ይቻላል።
አንዱ ቡድን ሌላውን በሙስና፣ በጎታችነት ወይም ደግሞ ህወሓትን በመክዳት… ወዘተ ይከሳል። የተወሰኑት ደግሞ በሁለቱ ካምፕ ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ከህዝብ ደብቆ ለመጓዝ እየጣሩ ቢሆንም፣ ችግሩ ግን ወደ ሕዝብ ጆሮ ደርሶ ፀሐይ ከሞቀው ውሎ አድሯል።
የዚህ ከፍፍል አንዱና ዋና ተዋናኝ የሆነው ስብሀት ነጋ ለመገናኛ ብዙሀን በቅርቡ በሰጠው መግለጫ በህወሓት/ ኢህአዴግ ውሰጥ ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌለና  ልዩነት ቢኖርም “በዴሞክራሲያዊ መንገድ” እንደሚፈታ ለመግለጽ ሞክሯል።  ይሁን እንጂ ወዲያውኑ “መለስን የሚተካ የህወሓት ሰው ለምን አልተገኘም? ለምን ሃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ ተመረጠ?” የሚል ከፍተኛ ጥያቄ በህዝቡ ውስጥ እንዳስነሳ ከትግራይ የሚተላለፈው ሬዲዮ በድንገት ሳያስበው አሰራጭቷል።

“ድህነታቸውን ህዝቡ ላይ አራግፈው ለራሳቸው ባለፎቆች ሆነዋል” ስማቸው ያልተገለጸ እናት



ሰሞኑን ከአገር ቤት አንዲት እናት ልጃቸውን ሊጠይቁ መተው ነበር። ልጃቸው የባለቤቴ ጓደኛ ነች።..የኔም ጓደኛ!…እኒህ አናት አንደበተ ርቱእና ተደምጠው የማይጠገቡ ጨዋታ አዋቂ ቀልደኛም ናቸው። ሑሉም ነገር የገባቸው ፍጹም ፖለቲካ አዋቂ ብሩህ እናት ናቸው። ጨዋታቸው ንግግራቸው ሁሉ ይማርካል። ሰማንያ አመት አይሞሉም። ጥንክር ያሉ፤ የነቁ ፍጹም ጤናማ እናት ናቸው።
ወይን ቢጤ ገዛሁና ባለቤቴ ድፎ ዳቦ ጋግራ (እናቶች አዚህ አገር ሲመጡ ድፎ ዳቦ ሲቀርብላቸው ደስ እንደሚላቸው ታውቃለች) እንኳን ደህና መጡ ልንል ሄድን።
ለሁለት ሰአት ያህል አብሬ ስቆይ ከናታችን የገበየሁት ትምህርትና ቁም ነገር በቀላል የሚገመት አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ እየጠላቸው ዛሬ ስልጣን ላይ የተጣበቁት የወያኔ ደናቁርት፤ addis-ababa-2013የኢትዮጵያን ህዝብ ምንም አያውቅም ብለው፤ የሚገምቱትና የሚንቁት፤ወደ ታች ወደ ህብረተሰቡ ዝቅ ብለው፤ስለነሱ አገዛዝ፤ ስለ መልካም አስተዳደር ያለውን ግንዛቤ ቢረዱ ምን ያህል ከህብረተሰቡ ኋላ ኋላ እየሄዱ እንመራሀለን እንደሚሉ በተረዱና ባፈሩ ይበጃቸው ነበር።
እኒህ እናት ድህነትን እኩል ያካፈለን ደርግ ተሻለ ነው ነው የሚሉት፤ “እነዚህ ድህነታቸውን ህዝቡ ላይ አራግፈው ለራሳቸው ባለፎቅ ሆነዋል። ደርግ አንዱን ልጅ አንዱን እንጀራ ልጅ አላደረገንም። ቢበድለንም አልለያየንም።”
ጎዳና ላይ ለፈሰሱ ለማኝ ህጻናትና ወላጆች ዘወትር ያለቅሳሉ። ኑሮአቸውን የከተማው ቆሻ ክምር ላይ የመሰረቱ ወላጆችና ልጆች ያስለቅሷቸዋል። “ይሄ ሁሉ ፎቅ ይገነባል። የእያንዳንዱን ፎቅ ባለቤት አስር አስር ልጅ ከጎዳና ወስዶ እንዲያሳድግ ቢያስገድዱት ጽድቅ ነበር። ላለው ሰው ምንም ማለት አይደለም” ይላሉ።

Monday, March 4, 2013

ከኬኒያው ፕሬዜዳንታዊ ምርጫ ምን እንማራለን?



East Arican Kenya election 2013
ለውጥ ፈላጊ ኬንያዊያን መራጮች ደምጽ ለመሰጠት ተራቸውን ሲጠባበቁ
ህዝባዊ  ምርጫዎች  በመጡ ቁጥር ስልጣኑን እነማን ይርከባሉ? ምርጫው ምን አዲስ  ነገር ይፈጥርልን ይሆን? ምርጫው ሰላም ወይም  አለመረጋጋት … ወዘተ ይቀሰቀስ ይሆን? የሚሉ መሰል  ጥያቄዎች በበርካታ መራጮች  አይምሮ ውስጥ መመላለሱ የተለመደ ነው፡፡
ከአምስት አመት (2007\2008 እ ኤ አ) በፊት ተካሄዶ  በነበረው  ፕሬዜዳንታዊ  ምርጫ ሳቢያ  ከ1300 በላይ ዜጎቿን ያጣች ፡ከ600ሺህ በላይ ዜጎቿ የተፈናቀሉባት  እና   በቤሊዮኖች  የአሜሪካ ዶላሮች  የሚገመቱ ንብረቶች  የወደሙባት  ጎረቤት አገር  ኬኒያ  በያዝነው  የፈረንጆቹ መጋቢት 4 2013 እኤአ ፕሬዜዳንታዊ  ምርጫ አድርጋለች፡፡ ከአንድ  ሳምንት በፊት በጋዜጠኞች አዘጋጅነት  ስምንት እጩ ፕሬዜዳንታዊ  ተመራጮች  ባደረጉት  3 ሰአት  የፈጀ የመጀመሪያው ዙር  ክርክር  በ34  ራዲዮኖች  እና  ስምንት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች  በቀጥታ ተተላልፋል፡፡ ይህ ከትምህርት  ፖሊሲ  አንስቶ  እስከ የዘር ማጥፋት  ወንጀል  ክስ  ድረስ  ያካተተው  ክርክር  ከ40ሚሊዮን  በላይ የሚገመተው  የኬኒያ  ህዝብን  ቀልብ ከመሳብ አልፎ አለማቀፋዊ  ትኩርትን  መሳቡ አልቀረም፡፡

ኢህአዴግ አሣ አስጋሪዎችን ጨፈጨፈ


የአሜሪካዊው አስከሬንና አሟሟት ሊመረመር ነው

የመከላከያ ሰራዊት በድንገተኛ ከበባ ከገደላቸው ንጹሃን ዜጎች መካከል የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን የአቶ ኡሞት ኡዶል ግድያ አስመልክቶ የአሜሪካ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ግድያው ከተፈጸመ በኋላ የሰራዊቱ አባላት አስከሬን አደባባይ በማውጣት ለህዝብ እያሳዩ ደስታቸውን ሲገልጹ የተመለከቱ የጋምቤላ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ክፉኛ መበሳጨታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጋምቤላ የደረቁን ወቅት ወይም በጋውን በወንዞች ዳር ውሃ ተንተርሶ መኖር የተለመደ ነው። ከቋሚ የመኖሪያ ቀዬ ወደ ወንዝ ዳርቻ በመሄድ አድኖ መመገብና አሳ አስግሮ ዕለትን ማሳለፍ የባህል ያህል ነው። በአገሬው ልምድ መሰረት ከቋሚ መኖሪያቸው ወደ ውሃ ዳር የሚሄዱት ወንዶች ሲሆኑ ጉዞውም የሚደረገው በቡድን ነው።Gambella
በዚሁ መሰረት በጋምቤላ ክልል የጎክዲፓች ነዋሪዎች የደረቁን ወቅት ለማሳለፍ በጊሎ ወንዝ ዳርቻ ወደምትገኘው አብሌን ያመራሉ። በቡድን ወደ አብሌን ያመሩት ሰዎች ከወንዝ አሳ በማስገርና ያገኙትን በማደን ቀን እየገፉ ሳለ የካቲት 21፤2005ዓም (28/2/13) በድንገት የመከላከያ ሰራዊት ከበባቸው። ተኩስ ተከፈተ። ለጊዜው ስድስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉንና የቆሰሉ እንዳሉ ለተጎጂዎቹ ቅርበት ያላቸው ያስረዳሉ።
ሰዎቹ ከጋምቤላ ከተማ 120 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አብሌን ተቀምጠው ኑሯቸውን እየገፉ ሳለ በድንገት የተከበቡት በጥቆማ እንደሆነ ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ያመለክታል። “አቶ ኡሞት ኡዶል እና ሌሎች መሳሪያ የታጠቁ አብሌን ታይተዋል” የሚል ጥቆማ የደረሰው ኢህአዴግ፤ ሰራዊቱን ሰዎቹ በቋሚነት ወደሚኖሩበት ጎክዲፓች በመላክ ቤተሰቦቻቸውን በመያዝ፣ በማሰርና፣ በመግረፍ ሰዎቹ ያሉበትን ቦታ እንዲያሳዩ አስገደዱ።