Tuesday, January 15, 2013

የአበበ ገላው ጉዳይ (ክንፉ አሰፋ)


ክንፉ አሰፋ

የአቶ መለስ ዜናዊ ዜና እረፍት በተሰማ ማግስት አንድ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵአዊ ከአውሮፓ ለአበበ ገላው ስልክ ይደውልለታል።  ግለሰቡ ደጋግሞ ሲደውል የአበበ የእጅ ስልክ ጠፍቶ ስለነበር ሶስት ተከታታይ የድምጽ መልእክቶችን ትቶ ነበር።
“አበበ እባክህን ባስቸኳይ መልሰህ ደውልልኝ።  አንተን በተመለከት ከአገርቤት የመጣ መረጃ አለ።እባክህን መልሰህ በዚህ ቁጥር አስቸኳይ ደውልልኝ።” ይላል መልእክቱ።  ደዋዩ ከልብ እንደተጨነቀ ከድምጹ መረዳት ይቻላል።
አበበም በተባለው ስልክ መልሶ ደወለ።

“ሄሎ! አበበ ገላው ነኝ::”

“ሃሎ! አበበ ገላው ነህ?”

“አዎ አበበ ነኝ፣ ማን ልበል?
“እኔን እንኳን አታውቀኝም፣ ***** እባላለሁ። የምደውልልህ በጣም ጠቃሚ መረጃ ልነግርህ ነው። ግዜ ካለህ አሁን ማውራት እንችላለን?”

“ችግር የለም ቀጥል።
“በረከት ስምዖን አዜብ መስፍን፣ እና ብረሃነ ገ/ክርስቶስ አንተን ለማስገደል ማቀዳቸውን ከውስጥ ሰው ተነግሮኛል። እጅግ በጣም የማምነው ከፍተኛ ስልጣን ያለው የደህንነት ሰው ነው የነገረኝ። አደራ ባስቸኳይ ንገረው ስላለኝ ነው ደጋግሜ የደወልኩት።  አንተን ለማስገደል ነብሰ-ገዳዮችን ወደ አሜሪካ ልከዋልና ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ….”
ደዋዩ ጉዳዩን ለአበበ ብዝርዝር አስረዳው።


አበበ ስልኩን እንደዝጋ የደዋዩን ማንነት ማጣራትና መረጃውን ማረጋገጥ ነበረበት።
በወቅቱ እኔም ቨረጂንያ ነበርኩና ከአበበ ጋር በጉዳዩ ተነጋገርን።  ስልክ ከአውሮፓ በመደወል መረጃ የሰጠው ሰው በቅርብ የማውቀው ወዳጄ ስለነበር፤ ሾልኮ የወጣውን ምስጢር ተአማኒነት በቀላሉ ለማረጋገጥ ቻልን።

መረጃው ትክክለኛ ይሁን እንጂ ነገሩን እንደዋዛ ነበረ ያለፍነው።  እነ አቶ በረከት ስምዖን በወቅቱ እጅግ ተበሳጭተው ስለነበር፤ ስሜታዊ ሆነው በዛቻ መልክ የተናገሩት ነበረ የመሰለን እነጂ እነዲህ አምርረው ነብሰ-ገዳዮችን አሜሪካ ድረስ ይልካሉ ብሎ ያሰበ አልነበረም።  በዚህ – አለም በመረጃ በተጠላለፈችበት ዘመን -  የኮ/ል ጋዳፊ የሎከረቢው አውሮፕላን ፍንዳታ አይነት ወንጀል ለመስራት ማሰብ ከእብደት ውጭ ምን ይባላል?

ያንን የወቅቱ  እብደታቸውን የተመለከተ አበበ ገላው ሃገር ውስጥ ቢሆን ስጋውን ዘልዝለው ሊበሉት እንደሚችሉ ጥርጥር አይኖርም። ለወያኔዎች ጋዜጠኛን መግደል አዲስ ነገር አይደለም።  የሉባር ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረው ተስፋዬ ታደሰን በሩ ላየ ነበር በሴንጢ ቆራርጥው በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉት። የወላፈን ጋዜጣ አዘጋጅም እስር ቤት ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሞት መደረጉ የሚረሳ ጉዳይ አየደለም።

አበበ ገላው በመለስ ላይ ያሰማው የተቃውሞ ድምጽ ህወሃቶችን ለምን በእጅጉ እንዳንገበገባቸው መገመት ግን ይቻላል።
“ፍሪደም! ፍሪደም! ፍሪደም!….” የሚለው የነጻነት ጩኸት በዚያች በካምፕ ዴቪድ/ሜሪላንድ የስብሰባ አዳራሽ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። አገር-ምድሩ ምስሉንና ድመጹን እየተቀባበለ ከማዳመጥ አልፎ በወቅቱ የሞባይል ፎን ሪነግ-ቶን ሆኖም ነበር።  የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንባገንኑ ስርዓት ላይ የነበረውን ፍርሃት የሚያስወግድና ለለውጥ እነዲነሳ የሚገፋፋ መልእክት ስለነበር እነ በረከትን ስጋት ውስጥ ሳይከታቸው አልቀረም።

አነባገነኖች ወትሮውንም ሌላዉን በበላይነት የመናገር እና በሃይል የማሳመን እነጂ የመስማት አቅም የላቸውም። ሌላውን እነዳሻቸው ይናገራሉ እነጂ ምላሽ አይፈልጉም። አንባገነኖች አፍ እነጂ ጆሮ የላቸውም። ስለዚህ ሰው ሲደፍራቸው አይችሉም። ያማቸዋል።   የአቶ መለስም ችግር ይኸው ነበር። በአንድ የተቃውሞ ድምጽ ተሰበሩ። በዚያ በሚያሞካሻቸው መሪ ፊት እንደ መብረቅ የወረደባቸው የማይወዱት መፈክር የስነ-ልቦና የበላይነታቸውን በማኮላሸት ውስጣዊ ማንነታቸውን ገደለው።
አንባገነኖች መሞት የሚጀምሩት በሃይል ያከማቹት በህዘብ ላይ የስነ-ልቦና የበላይነት ሲኮማሸሽ ነው። ይህ ደግሞ የማይድን በሽታ ነው። የደፈራቸውን ሰው ካልገደሉ በሽታው አይለቃቸውም።

ይህንን አባባል የቬጋሱ ገጣሚ ጌታቸው አበራ ‘ የፓርላማ ድንፋታ-በዲሲ ተረታ!’  በሚለው ግጥሙ በደንብ ገልጾታል።

ሁለት አሥርት ሙሉ “ያለኔ ማን” ያለ፣
ከራሱ “ራሶች” ጋር ፓርላማ የፎለለ፣
ቢባል…ቢባል…ቢጻፍ…አልሰማ ቢል ከቶ፣
አበበ ነገረው፤ በ”ማዕረጉ” ጠርቶ።
(ራሱን ላዋረደ ክብሩን ለናቀ ሰው፣ “ዲክታተር” የሚለው “ማዕረጉ” ሲያንሰው ነው።)
በብረት ተከቦ — ራሱን አጉል ክቦ፣
በውዳሴ ዜማ — ባጎንባሽ ታጅቦ፣
አገር ያዋረደ፣ ሕዝብን ያሳደደ…
ሰው መሳይ በሸንጎ፣
እማያቁት አገር “ቁርበት አስነጥፎ” ሊበላ ፈልጎ፣
“ፐርሰንቱን” ሲጠቅስ ሃሳዊው መሲህ ሊቅ፣
ፓርላማ ያለ መስሎት ጭብጨባ ሲጠብቅ፣
ሲሸሽ የኖረውን፣ ሰምቶ እማያውቀውን፣
እስኪሰበር ቅስሙ አገኘው ዋጋውን።
የአበበ ገላው የካምፕ ዴቪድ ተቃውሞ ለአቶ መለስ ሞት ምክንያት ይሁንም አይሁን ሌላ ምርምር የሚጥይቅ ጉዳይ ነው። ይኽ ክስትት ግን ራሱ አበበ ገላው ነጻነቱን እንዲያጣ አድርጎታል። ይህንን ያስተዋልኩት አንድ ምሽት አበበ ገላው ከሌሎች የኢሳት ባልደረቦች ጋር በመሆን ቨረጂንያ የሚገኝ የአበሻ ምግብ ቤት ቁጭ እንዳልን ነበር። ምግብ ቤቱ ጢም ብሎ በአበሻ ታዳሚዎች ሞልቷል። ያለማጋነን የሁሉም ደንበኞች አይን እኛ ካለነበት ጠረጴዛ ላይ አነጣጥሯል። አነዳነዶች ሲጠቋቆሙ ይታያሉ። ሌሎች ደግሞ የመለስ ገዳይ ሲሉ ይሰማል።  ከመቀመጫቸው እየተነሱ የአድናቆትና የማክበር ሰላምታ የሚስጡ ሰዎች ቁጥርም ቀላል አልነበረም። ወዳጅ እና ጠላት በውል በማይለይበት ሁኔታ እዚያ ስፍራ መቆየቱን ስላልወደድን – አበሻ በብዛት ወደማይገኝበት ወደ ሂልተን ሆቴል ማምራት ግድ ሆነብን …

የጆርጅ ኦርዌል Nineteen Eighty-Four መድብል ታወሰኝ። ኦርዌል ‘Freedom is slavery’ ነበር ያለው – በተቃርኗዊ አገላለጽ። በኦሺንያ ግዛት ህዝቡ በአንድ ፓርቲ አንባገነን አገዛዝ ስር ወድቆ ምን ያህል የስነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ እንደገባ ነበር ኦርዌል የጻፈው። አንድ ሰው ብቻውን ትልቅ ህንጻ መገንባት አይቻለውም።
“በዚህች ምድር ላይ ያለን አነዱና ትልቁ ነገር ነጻነት ነው።” ያሉት ዊንስተን ቸርችል ነበሩ።  በእረግጥም ነጻነት ቀላል ነገር ነው። በነጻ  ግን አይገኝም።  ለሌላው ነጻነት የአንዱ  መስዋዕት መሆን ግድ ነው። እነ ማረቲን ሉተር፣ እነ ማንዴላ ፣ እነ ፋራካን፣ እነ ማልኮም ኤክስ፣ እነ ጋንዲ እነ ፕ/ር አስራት ወልደየስ… ሁሉም ለሰው ልጆች ነጻነት ሲሉ ነጻነታቸውን ያጡ የምድራችን ልዩ ፍጡራን ናቸው።

ነጻነት ምርጫ እነጂ ስጦታ አይደለም።  ማልኮሜክስ እነዲህ ይላል። “ነጻነትህን ማንም ሰው በቸርነት አይሰጥህም። ሰው ከሆንክ ነጻነተህን አንተው ራስህ ውሰድ።” አበበ ገላው፤ ፈረንጆቹ ፕራይቬሲ የሚሉትን የግል ነጻነቱን ይጣ እነጂ የሚሊዮኖች ድምጽ በመሆን የነጻነትን ጩኸት በአለም መድረክ ማስተጋባቱ ሊያኮራው ይገባል። ቢያንስ የማይረሳ ታሪክ ሰርቷል። ይህ ወንድማችን በሰራው ሰላማዊ ስራ፤ ከራሱ ነጻነት ማጣት ባሻገር ሌላ መስዋእት ቢከፍልም የሚቆጨው አይደለም። መስሏቸው ይሆናል እነጂ እነ በረከት አበበን ሊያስገደሉ ቢችሉ እንኳን በሕዝብ አእምሮ የተቀረጸውን፤  ያን የነጻነት ድምጽ  ሊያጠፉት አይችሉም።
ነብሰ-ገዳዮቹ ተሳክቶላቸው ቢሆን ኖሮ፤ የሚሞተው አበበ ገላው አልነበረም። ሞቱ የሁላችንም ይሆን ነበር። የደጋፊው ቁጥር ከወንበዴው በመቶ እጥፍ ቢበልጥም ተግባር ላይ ኢትዮጵያዊው ችግር ይታይበታል። ይህም ጠንካራ የተደራጀ ሃይል ካለመኖር የሚከሰት ችግር ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ የሶርያ ኮሚኒቲ ጠንካራ በመሆኑ ስደተኞችን እየሰለሉ ለአነባገነኑ ባሽር አላሳድ አሳልፈው የሚሰጡ ካድሬዎችን በመከታተልና በማስያዝ የበዙዎችን ህይወት ከአንባገነኑ ጥርስ አትርፈዋል። ሰላዮችንም ከኤፍ. ቢ. አይ. ጋር በመተባበር እንዲታሰሩ አድርጓል። የኢትዮጵያ ዲያስፖራም ለራሱ መብት ሲል መሰባሰብ፡ መወያየት እና ጠንክሮ መታየት ይኖርበታል።

ልብ እንበል። ዛሬ በአበበ ገላው የተጀመረ የግድያ ሙከራ ነገ በሌላው ላይ እንደሚቀጥል ምንም ጥርጣሬ የለውም። የእነበረከት ቅጥረኞች ስምንት ሺህ ማይል ድረስ አቋርጠው ለከባድ ወንጀል መሰማራታቸው በአሜሪካ መንግስት ብቻ ሳይሆን፡ በዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ላይ ያላቸው ንቀት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ያሳየናል። የአበበ ገላው ጉዳይ የኛ የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነው።

ጸሁፌን እንደተለመደው በቀልድ ልቋጭ። በዚያን  ወቅት እነዲህ ተባለ።
አቶ መለስ የወትሮ ህመማቸው ተባብሶ ቤልጅየም ሆሰፒታል እንደደረሱ ሃኪማቸው ከፉኛ ደንግጦ አነድ ሀሳብ አቀረበላቸው።
“ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የጭንቅላትዎ እጢ እድገቱ በጣም ጨምሯል። … በኦፕሪሽን ተቆርጦ መውጣት አለበት። ያም ሆኖ የመትረፍ እድሎ …”

አቶ መለስ የዶክተሩን ንግግር በመሃል በማቋረጥ።
“እባክህ እሱን ተወውና የአበበ ገላውን ድምጽ ከጭንቅላቴ አውጣልኝ።” ብለውት ነበር ይባላል።

***

ነብሳቸውን ይማረውና አቡነ ጳውሎስም አቶ መለስ ከምድረ አሜሪካ እንደተመለሱ ጸበል ብጤ ሞክረውላቸው ነበር ይባላል። አባ ጳውሎስ ስራቸውን ጀመሩ፣

“ጠቅላይ ሚኒሰትሩን እነዲህ ጨምድደህ የያዝከው ለመሆኑ አንተ ማን ነህ!”
“አበበ ገላው ነኝ።”
“አሁን ትለቃለህ አትለቅም?”
“አልለቅቅም!”
“…ልቀቅ!”
“አልለቅቅም! መጀመርያ እሱ ይልቀቅ።”

No comments:

Post a Comment