የመረጃ ቴክኖሎጂ መሠረት የሆነዉ የቴሌኮሚኒኬሺን ዘርፍ አፍሪካ፤ ላቲን አሜሪካና ኢሲያ ዉስጥ የሚገኙ በእደገት ወደ ኋላ የቀሩ አገሮችን ለዘመናት ከተዘፈቁበት የኋለ ቀርነት ማጥ
ዉስጥ ጎትቶ አዉጥቶ ወደ ፈጣን የእድገት ጎዳና ይወስዳቸዋል ተበሎ የታመነበትና በአንዳንድ አገሮች ዉስጥ ይህ ለእድገት አመቺነቱ በተግባር የተመሰከረለት ዘርፍ ነዉ። ይህ ዘርፍ ገበሬዉ፤ ሰራተኛዉ፤ ተማሪዉ፤ ወታደሩና ለሌላም በማንኛዉም የስራ ዘርፍ ለተሰማራ የህብረተሰብ ክፍል የእዉቀት ምንጭ በመሆን የስራ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ የሚረደና በህብረተሰብ መካከል ፈጣን የሆነ የመረጃ ልዉዉጥ አንዲኖር የሚያደርግ ዘርፍ ነዉ። በእድገት ወደ ኋላ ለቀረችዉ አገራችን ኢትዮጵያም ይሀ ዘርፍ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ ዘርፍ ነዉ። ነገር ግን በአፍሪካ ዉስጥ አገራችን ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ወደኋላ ከቀርችባቸዉና ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ ሆን ብሎ እድገታቸዉ እንዲገታ ካደረጋቸዉ ኋላ ቀር ዘርፎች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ይሄዉ የቴሌኮሚኒኬሺን ዘርፍ ነዉ።
እራሱን “ልማታዊ መንግስት” ብሎ የሚጠራዉ የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ከያዘባቸዉ የመጀመሪያዎቹ አመታት ጀምሮ አስከ ቅርብ ግዜ ድረስ እንደ ቤት ዉስጥ ዕቃዉ ከተቆጣጠራቸዉና የኢትዮጵያን ህዝብ በሚጠቅም መልኩ እንዳያድጉ ካደረጋቸዉ ቁልፍ መስሪያ ቤቶች ዉስጥ አንዱ ኢትዮቴሌኮም ነዉ። ወያኔ ኢትዮቴሌኮምን ያላደረገዉ ነገር የለም። ዘረኝነትን በሚጠቅም መልኩ አደራጅቶታል፤ የራሱን ሰዎች ጠቅጥቆበታል፤ ቻይናዎችን አምጥቶ የስለላ ተቋም አድርጎታል፤ የሚገርመዉ ዛሬ ኢትዮቴሌኮም የተራቀቀዉ በስልክ፤ በኢንተርኔትና በሌሎችም የመገናና አገልግሎቶች ሳይሆን ዜጎችን በመሰለልና የመረጃ ጨለማ በመፍጠር ርካሽና ጎታች ስራዎች ነዉ። ይህንን ርካሽ ስራ ደግሞ በቅርቡ የአገዛዙ የኢንፎርሜሺን ደህንነት ኤጀንሲ ሹም ብ/ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ “የኢትዮጽያ ቴሌኮምኒኬሽን” የኀብረተሰቡን ሰላም የሚያጠፉ ዌብሳይቶችን የመቆጣጠርና የኢንተርኔት ድረገጾችና ብሎጎችን የማገድ አቅም ሊኖረው ይገባል፡፡መርሁም ይህ ነዉ በማለት በአዳባባይ አረጋግጧል።