Tuesday, November 12, 2013

”ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ሊቀይር ከቶ ይቻለዋልን?”





ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር

ዥንጉርጉርነቱን ሊቀይር
ከቶ ይቻለዋልን?”
(ትንቢተ ኤርምያስ 13:23)

                                                                                                                                     
 -ከምናሴ መስፍን - ኖርዌይ
በዚች ባለንበት ፕላኔት ላይ የሰው ልጅን አስተሳሰብ ወይም ህገ ልቦና ከሚዳኙት ረቂቅ ክንውኖች መሀከል የስነ መለኮት ወይም የስነ ፅሁፍ ሀብቶች ውስጥ ታላቁ መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ) አቢዩ ነው። ታላቁ  ይናገራል።
ምንም እንኩዋን በአገራችን የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ዘመቻ - ከውጭም ሆነ ከውስጥ እኩይ ጡት ነካሽ ልጆችዋም የሚሰነዘሩ፤ ዘርፈ ብዙ እርሷነትዋን የማጥፋት ዘመቻዎች እጅግ ይበዛሉ፡፡ ያም ሆኖ እነርሱ እራሳቸው እንቅልፍ ያጣሉ እንጅ አምላክ በቃል ኪዳኑ ስለሚጠብቃት አንዳች አትሆንም።
አንዳንድ የታሪክ ጸሀፊዎችና እግዚአብሄርን የማያውቁ ሃቁን በማዛባት እግዚአብሄር ከላይ የሠራትን ቃል ኪዳናዊት ኢትዮጵያን ለማጥፋት ብዙ ቢዳክሩም ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ አገራችን ህልውናዋ ከላይ ከሰማይ የታወጀና በዚህም ማንነቷ ታውቃ የኖረችና ወደፊትም የምትኖር ሉአላዊት ሀገር ነች። 
በርካታ የክርስትና ኃይማኖት አባቶች ስለኢትዮጵያ ማንነት በሚጽፏቸው መጻህፍት ውስጥ ኢትዮጵያንና እርሷ ስትጋደልላቸው የኖረችውን መለኮታውያን ይዞታዎቿን ለማፈራረስ ሲታገሉ የነበሩ ጠላቶችዋ ብዙ ናቸው፡፡ እኒህ ደመኛ ያገሪቱ ጠላቶች ካሳፋሪ ድርጊታቸው ያታቀቡ ዘንድ፤ በኃያሉ እግዚአብሄር ፊት ንስሃ ገብተው ከእኩይ ዓላማቸው እንዲመለሱ ምጻኔ ተደርጓል፡፡
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ እጅግ መጠነ ሠፊ ጥቃቶች ተሰንዝረውባት በርካታ መከራዎችን አስተናግዳለች። ጥቃቱ የሕዝቡን ሕይወት ጭምር አጥፍቷል። በሁሉም የመከራ ዘመናት ግን የእግዚአብሄር መለኮታዊ ጥበቃ ህያው ነው። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለማጥፋት ዲያብሎስ የተጠቀማቸውን የእስከዛሬውን ሶስት እኩይ የታሪክ ክንውኖች እስኪ እንቃኝ።
የመጀመሪያው ዮዲት ወይም ጉዲት በምትባል ኢትዮጵያዊት ንግሥት የተፈጸመ ነው። ይህችው ንግሥት 960 . . አክሱም ድረስ በመሄድ ደብረዳሞን ጨምሮ በርካታ አብያተ ክርስትያናትን አውድማ፣ ቅርሶችን አቃጥላ ነዋሪውን በእሳት አቃጥላ ፈጅታለች። ዮዲት ኢትዮጵያዊውን የአክሱም ሥርወ መንግስቱን ደምስሣ በምትኩ የራስዋን አስተዳደር መሥርታለች ይባላል። አንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች ጉዲት ከኤርትራ ክልል የመጣችና ከአገው ሕዝብ የተገኘች ቤተ እስራኤላዊ ነች ይላሉ።
ሁለተኛው ትልቁ የእትዮጵያ መከራ የተንሰራፋው የነቢዩ መሃመድን ኢትዮጵያን እንዳትነኩ ትዕዛዝን ባለማክበር አህመድ ግራኝ የተባለ ጦረኛ ከምስራቅ ኢትዮጵያ በመነሳት ክርስትና ኃይማኖትን ለማጥፋት ጦር ሰብቆ የተነሳበት ጉዳይ ነበር። 1528 . . አህመድ ግራኝ በሸዋ፣ በጎንደር፤ በወሎና በትግራይ ይገኙ የነበሩ አብያተ ክርስትያናትን በማቃጠል ክርስትያኑን ፈጅቶ መንግስቱን አቃወሰ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበሩት አጼ ልብነ ድንግል ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ሲዋጉ ብዙ ሕዝብ አልቆባቸዋል። አጼ ልብነ ድንግል የፖርቱጋሎቹን ርዳታ ቢጠይቁም እንኳን በአፋጣኝ ስላልደረሰላቸው ትግራይ ውስጥ በሚገኘው ደብረዳሞ ገዳም ውስጥ ተሸሸገው እንዳሉ እዚያው ሕይወታቸው አልፋለች። 1543 . . የአጼ ልብነ ድንግል ልጅ አጼ ገላውዲዎስ ዙፋኑን ከወረሰ በኋላ ውጊያውን በማፋፋም ግራኝን ጣና ሃይቅ አካባቢ ድባቅ በመምታት የሀገሪቱን ኅልውና ዳግም በማደስና ክርስቲያኑን በማነጽ የወደሙትን ቤተ ክርስትያናትን መገንባት ጀመሩ። 1559 አጼ ገላውዲዎስ ሃረር ላይ ዘምተው በጦርነቱ ላይ ሞቱ። በዚሁ የመከራ ዘመን በርካታ ነዋሪዎች የትውልድ አካባቢያቸውን በመልቀቅና በመሰደድ መቶ ዓመታት ያህል ለሰነበተው የኃይማኖትና የመስፋፋቱ ጦርነት ሰላባ ሆነዋል።
የጉልታዊው ጭቆና ሥርዓት ምሬት የወለደው 1966 . . የሕዝብ አብዮት እግዚአብሄር አልባ በሆኑ ወታደራዊ ኮሙኒስቶች ሥር ወድቆ ሀገሪቱን ፍዳ ሲያበላ ቆይቶ አስራ ሰባተኛ ዓመቱ ላይ ራሱን አጠፋ። ክርስቲያኖቹና እስላሞቹ ባሳዩት የማይበገር ጽናት ይህ የክህደት ዘመን ከተገረሰሰ በኋላ፤ ወታደራዊ መኮንኖቹን የተኩት ወያኔዎች ይበልጡኑ እግዚአብሄር አልባ ሆነው ብቅ አሉ፡፡ ከዮዲት ጉዲትና ግራኝ መሀመድ ባልተናነሰ ሀገሪቱን ለማጥፋት በዘር ክልል ሸንሽነው ለሶስተኛ ጊዜ ታሪክ የመዘገበው የሕዝብ መከራ እንደገና እውን ሆነ።
ወያኔ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ፈጽሞ የሌለና የተሳሳተ ትርጉም በመስጠት፤ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንዲራዋን ምስጢር ሳይቀር  በማጉደፍ ጠላትዎቿን ጭምር አስደስቷል። በእርግጥ በመጀመሪያ በዮዲት ጉዲት ኋላ በግራኝ መሀመድ ያልጠፋች ሀገር በወያኔዎቹ ግፍና ሰቆቃ ልትጠፋ ባትችልም እንኳን ለጊዜውም ቢሆን የሕዝቡ አንድነትና ፍቅር እጅግ ፈተና ውስጥ ወድቋል። ኢትዮጵያ ወደቧ ተወስዷል። መሬቷ ላባዕዳን ቱጃሮች እየተቸረቸረ ሕዝቡ ቀዬውን እንዲለቅ ተፈርዶበታል። በዚሁ የሶስተኛው የጥፋት ዘመን ሃገሪቱን በደማቸው ዋጅተው ድንበሯን አስከብረው ነጻነቷን ያደመቁት አማሮች ልጆቻቸውና የልጅ ልጅ ልጆቻቸው በጠላት ተፈርጀው ሕጻናት፣ ወጣት፣ ሽማግሌ፣ አሮጊት ሳይቀር በበደኖና አርባጉጉ ጥልቅ ገደሎች ተወርውረዋል። ግፉ ቀጥሎ ከደቡብ ኢትዮጵያ ጉራ ፈርዳ ዞን እጅግ በርካታ አማራ አርሶ አደሮች እንዲሁም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ በርካታ ቁጥር ያላቸው አማሮች እንዲፈናቀሉ ተደርጓል። ይህ የአማራውን ዘር ነጥሎ የማጥፋቱ የወያኔው እኩይ ዓላማ ነገ ወደ ተቀሩት አካባቢዎች ላለመደገሙ አንዳች ዋስትና የለም።
ኢትዮጵያውያን ማናቸውንም ስቃይና ግፍ በትእግስት ተቋቁማ እግዚአብሄርን በሕይወታቸው በሚያንጸባርቁት ልጆቿ በመታገዝ ዳግም ከፍ ትላለች። በእርግጥ በዚህ ግለኝነት በተንሰራፋበት፣ ስደት እንደ ኑሮ አማራጭ በተቆጠረበት፣ የወገኑ ስቃይ ያልተሰማው ቤተ ሠሪው በዝቶ ሠርግና ምላሹ ቅጡን ሲያጣ ብዙዎች ከትግል ቢዘናጉም ረቂቁ የእግዚአብሄር ሃይልና የጥቂቶቹ የእግዚአብሄር ሰዎች ልባዊ ጸሎት ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ጠብቆ እንደ ብረት ያጸናታል።
የዮዲት ጉዲት ፍጅት፣ የግራኝ መሀመድ ወረራና የወያኔው የዘር ማጥፋቱ ግፍ ሶስቱም ሰቆቃዎች የተፈጸሙት በናት ጡት ነካሽ ልጆችዋ ነው። ነብር ዥንጉርጉርነቱን መለወጥ የሚችል ኃይል እንደሌለ ሁሉ ኢትዮጵያዊውን መልኩን የሚለውጥ፣ እምነቱን የሚያዛንፍ፣ ቅን አመለካከቱን የሚያሻክር፣ ትዕግስቱን የሚያሸንፍ ስነ መንግስታዊ ፈሊጦቻቸውን ማጽናት ግን አልቻሉም። በእርግጥ ከባዕዳኑ ወረራ ይልቅ ኢትዮጵያን እጅግ የሚያቆስሏት የቀን ጅቦቹ፣ ከሃዲዎቹና ሆዳሞቹ ለጊዜው ፈተናዋን ያበዙታል።
ወያኔና አሳዳጊው ሻእቢያ ይህን ሁሉ ግፍና ሰቆቃ በድፍረት የፈጸሙት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለማጥፋት ቢሆንም እኛ ማጎብደዱን ትተን ግፉን መቀበል ስናቆም እግዚአብሄር ዓላማቸው ከስር ጀምሮ ይንዳል።
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ይሁን
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች - (መዝሙር 68:31)
            
                                          ጸሃፊውን በዚህ አድራሻ ማግኘት ትችላላችሁ menasse11@gmail.com


1 comment:

  1. Trying to put EPRDF in the same position as ahmed gragn or yodit and making it look like
    woyane is committing a genocide is so much irresponsible . You should know that accusing
    the ethiopian government with such atrocious nomenclature will have consequences and you
    will pay the price for that.

    ReplyDelete