(ecadforum.com ኢዲቶሪያል)
ሰሞኑን ወያኔ/ኢህአዴግ በህግ ተመዝግበው በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን ለማጥፋትና በመጪው ምርጫ ላይ እንዳይሳተፉ ለማድረግ በርትቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
እስካሁን መኢሕአድ እና አንድነት ፓርቲ የዚሁ የወያኔ/ኢሕአዴግ የቅድመ ምርጫ “ተቃዋሚዎችን የማዳከም እና የማጥፋት ዘመቻ” ሰለባ ሆነዋል።
በቅርቡ ራድዮ ፋና እና ኢቲቪ ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ጋር አድርገውት የነበረውን ቃለ-ምልልስ (በኋላ የቃለ-ምልልሱ ድምጽ ጠፋብን ማለታቸው ይታወሳል፣ ይሁንና ኢሳት ቴሌቪዥን ጠፋ የተባለው ቃለ-ምልልስ በእጁ ገብቶ ኖሮ እያሰራጨው ይገኛል) ቃለ-ምልልሱን ለማዳመጥ እዚህ ይጫኑ። ከቃለ-ምልልሱ መረዳት እንደሚቻለው ፖሊስ ቀመሱ የወያኔ/ኢሕአዴግ ጋዜጠኛ ምን ያህል ሰማያዊ ፓርቲን የሚያስወነጅሉ ነገሮች ፍለጋ ይባዝን እንደነበር ነው። ይህ የሚያመለክተው ሰማያዊ ፓርቲ ቀጣዩ የወያኔ/ኢህአዴግ “ተቃዋሚዎችን የማዳከም እና የማጥፋት ዘመቻ” ሰለባ እንደሚሆን ነው።
ወደ ተነሳንበት ርዕስ ስንመለስ፣ ከላይ የተጠቀሱትን ሁነቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አንዳንድ በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ ፖለቲከኞች እና ለውጥ አራማጆች “ወያኔ/ኢሕአዴግ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን እያቀጨጨ ነው፣ ገዢው ፓርቲ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን እያጠፋ ነው፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አከተመለት…” ሲሉ ይደመጣሉ።